
ባሕርዳር፡ መስከረም 15/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል የመስቀልና የመውሊድ በዓላት ሰላማቸው ተጠብቆ እንዲከበሩ በቂ ዝግጅት መደረጉን የክልሉ የኮማንድ ፖስቱ አባልና የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ደስዬ ደጀን አስታወቁ።
ኮሚሽነር ደስዬ ደጀን ዛሬ በሰጡት መግለጫ ፤ በዓላቱ በሰላም ተከብረው እንዲጠናቀቁ አስፈላጊው ዝግጅት መደረጉን አስታውቀዋል።
በዝግጅቱም ኮማንድ ፖስቱና በክልሉ እስከ ታች ያለው የፖሊስ መዋቅር ከሌሎች የጸጥታ ኀይሎች ጋር በመተባበር ወደ ሥራ መገባቱን ገልጸዋል።
ኮማንድ ፖስቱና ፖሊስ በበዓላቱ አከባበር ወቅት የሕዝብን ሰላምና ደህንነት የማስጠበቅ ተልዕኳቸውን በተገቢው ለማከናወን ዝግጁ መሆናቸውን አረጋግጠዋል።
ኮሚሽነሩ በማያያዝም በተለይም በአደባባይና በየአካባቢው የደመራ ሥነ-ሥርዓት የሚከበረው የመስቀል በዓል ጋር በተያያዘ የእሳት አደጋ እንዳይከሰት ምዕመኑ ተገቢውን ጥንቃቄ ማድረግ እንዳለበት አሳስበዋል።
መላው የክልሉ ሕዝብም ከበዓላቱ ሃይማኖታዊና ባህላዊ ክዋኔ ውጪ የሆኑ እንቅስቃሴዎችን ሲመለከት በየአቅራቢያው በተጠንቀቅ ላይ ለሚገኝ የጸጥታ ኀይል በመጠቆም ተገቢውን ትብብርና ድጋፍ እንዲያደርግ ኮሚሽነሩ ጠይቀዋል።
ኮሚሽነሩ ለክርስትናና ለእስልምና እምነት ተከታዮች ለመስቀልና ለመውሊድ በዓላት የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
 
             
  
		