ኢስላም- የዓለም ሰላም!

31

ባሕር ዳር: መስከረም 15/2015 ዓ.ም (አሚኮ) ስለ እስልምና በቅድስቲቱ ከተማ መካ ለነዋሪዎቹ ጥሪ ከመደረጉ አስቀድሞ አካባቢው እና ነዋሪዎቹ የበዛ ቁጥር ያላቸውን እና የተለያየ ደረጃ የተቀመጠላቸውን ጣኦታት ያመልኩ እንደነበር ይነገራል፡፡ በተለይም በመካ እና በአካባቢው ከ360 በላይ ቁጥር ያላቸው ጣኦታት በየስፍራው ተሰራጭተው ለአምልኮ እንደ አምላክ፤ ለፍጡር እንደ ፈጣሪ ተደርገው ይመለኩ ነበር ይባላል፡፡ የሚገርመው ደግሞ ጣኦታቱ እንደ አምላኪዎቹ የኑሮ ደረጃ የተለያየ የክብር እርከን የነበራቸው መኾኑ ነው፡፡

ሀገረ ገዢዎች እና በሃብት ደረጃቸው ጣራ የነኩ ቱጃሮች ከወርቅ የተሠራ ጣኦት ሲዘጋጅላቸው፤ በሁሉም መመዘኛ መለስተኛ የሚባሉት ከብር የተዘጋጀ ጣኦት እና ከእነርሱ ዝቅ ያሉት ደግሞ ከነሐስ የተሠሩ ጣኦታት ተዘጋጅቶላቸው ያመልኳቸው ነበር፡፡ ድሆች በአንጻሩ ከእንጨት የተሠሩ ጣኦታት እንደነበሯቸውም ይነገራል፡፡ የጣኦታት አምልኮን አፍርሶ በአንድ አሏህ ፈጣሪነት እንዲያምኑ ለማድረግ የነብዩ ሙሐመድ (ሰ.ዐ.ወ) መልዕክተኛ ኾኖ መምጣትን የግድ ይጠይቅ ነበር፡፡

ከነብዩ ሙሐመድ (ሰ.ዐ.ወ) መምጣት በፊት ምድሪቷ 123 ሺህ ነብያትን እና 313 መልዕክተኞችን አስተናግዳ ነበር ያሉን የኢትዮ ዓረብ የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት ተመራማሪው ፕሮፌሰር አደም ካሚል ናቸው፡፡ ነገር ግን የመጡት ነብያት እና መልዕክተኞች ሁሉ በየመጡበት ብሔር እና ጎሳ የሚላኩ እንጂ ዓለም አቀፋዊ ተልዕኮን እና ውክልናን የተላበሱ አልነበሩም ይላሉ፡፡

ከነብያችን በፊት የመጡት ነብያት እና መልዕክተኞች ሁሉ ተልዕኳቸው ክልላዊ፣ አካባቢያዊ ፣ ብሔራዊ እና ጎሳዊ ነበር የሚሉት ተመራማሪው የሰውን ልጅ በምድር ላይ ወኪል ያደረገ የአሏህ መልዕክተኛ ያስፈልግ ስለበር ነብዩ ሙሐመድን (ሰ.ዐ.ወ) መልእክተኛ አድርጎ አሏህ ላካቸው ፤ ለእስልምና ትልቅ መሰረት ነበር ይላሉ፡፡

በወርሃ ሩቢዑል አወል 570 ላይ ይህችን ምድር የተቀላቀሉት ነብዩ ሙሐመድ (ሰ.ዐ.ወ) ከእናታቸው ማህጸን ጀምሮ ተዓምራትን ያሳዩ ተወዳጅ ነቢይ እንደነበሩ ይነገራል፡፡ አባታቸውን ገና በማህጸን ውስጥ ሳሉ ያጡት ነብይ እንኳን የአሏህ እዝነት እና ፈቃድ ተጨምሮበት የሕይዎት መንገዳቸው ብቻ በራሱ አስተማሪ ነበር ይባላል፡፡

ነብዩ ሙሐመድ (ሰ.ዐ.ወ) ገና ስድስት ዓመት ሲሞላቸው የአባታቸውን መቃብር ሊዘይሩ ወደ መዲና ከእናታቸው እና ከኢትዮጵያዊት አሳዳጊያቸው ጋር አቀኑ፡፡ ነገር ግን ከመዲና ሲመለሱ ልክ እንደ አባታቸው ሁሉ እናታቸውንም በሞት ተነጠቁ፡፡ አባትን በማህጸን እናትን በምድረ በዳ ሳሉ በሞት የተነጠቁት ነብይ የልጅነት ጊዜያቸውን ከአያት ወደ አጎት እየተመላለሱ አሳለፉት፡፡

በዘመነ ሒጅራ 610 ላይ ነብዩ ሙሐመድ (ሰ.ዐ.ወ) 40 ዓመት እንደሞላቸው ከአሏህ አዲስ አዋጅ እና ትዕዛዝ ተላለፈ የሚሉት ፕሮፌሰር አደም እርሱም 114 ምዕራፎች ያሉትን የመጀመሪያው ቁርአን በመላዒካው ጅብሪል አማካኝነት ወረደላቸው፡፡ ለተከታታይ ሦስት ዓመታትም ወደ ዋሻ እየተመላለሱ አምላካቸውን አሏህ በፍጹም ሰላም እና ትህትና አገለገሉት፡፡

እንደ ፕሮፌሰር አደም ገለጻ ነብዩ ሙሐመድ (ሰ.ዐ.ወ) በ613 ዘመነ ሒጅራ ላይ “የተሰጠህን ሙሉ ኅላፊነት ተወጣ የሚል” አስቸኳይ ትዕዛዝ ደረሳቸው፡፡ ይኽንን አስቸኳይ አዋጅ እና ትዕዛዝ ተከትሎ ነብዩ ሙሐመድ (ሰ.ዐ.ወ) ለሕዝቡ ጥሪ በማድረግ በጣኦታት ማምለክን ትታችሁ አንድ አሏህን ወደማምለክ ተመለሱ የሚል አስተምህሮን አስተጋቡ፡፡ የበዙ ተከታዮች ማሰባሰብ ቢችሉም ነገሮች ግን አልጋ በአልጋ አልኾኑላቸውም ነበር፡፡

ጥላቻው፣ ማሳደዱ፣ ዘረፋው እና ነቀፋው በአሏህ መልዕክተኛ እና ተከታዮቻቸው ዘንድ ወረደ፡፡ ግድያው እና ማሳደዱ ሲበረታም የተወሰኑትን በዘመኑ ቅዱሳን ወዳሏቸው ሀገራት ዘንድ ክፉ ጊዜያትን እንዲያሳልፉ እስከ መላክ እና ማሸሽ ደረሱ፡፡ ያም ኾኖ ግን የዓለም ሰላም የኾነውን ሃይማኖታዊ አስተምህሮ ከመምጣት የሚያግደው አልነበረም፡፡ እስልምና መነሻው ከኾነው የዓረቡ ዓለም ወጥቶ ድፍን ዓለምን ማዳረስ ቻለ፡፡

“ኢስላም አስተምህሮው ሰላም ነው” የሚሉት ፕሮፌሰር አደም ዛሬ ላይ እስልምና ውጣ ውረዱን ሁሉ አልፎ ከአንዱ አጽናፍ እስከ ሌላኛው አጽናፍ የተዘረጋ ሃይማኖት ኾኗል፡፡ በአሏህ ፈቃድ የምድራችን የመጀመሪያው ዓለም አቀፍ መልዕክተኛ እና የመጨረሻው ነብይ እስልምናን ዋጋ ከፍለው ለብዙዎች የሕይዎት ብርሃን ይኾን ዘንድ መሰረት ጥለውለታል፡፡ የነብዩ ልደት ሲከበርም ይሕንን የነብዩን ኢስላማዊ አበርክቶ ለማስታወስ ያለመ ነው ይላሉ ፕሮፌሰሩ፡፡

ዘጋቢ፡- ታዘብ አራጋው

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“በጀት ዓመቱ ከ22 ሺህ በላይ የሥራ ዕድል ለመፍጠር እየሠራሁ ነው” የደብረብርሃን ከተማ አሥተዳደር ሥራ እና ሥልጠና መምሪያ
Next articleከሰሞኑ በተፈጠረው የፀጥታ አለመረጋጋት የንብረት ውድመት መድረሱን የአንኮበር ወረዳ ገለጸ፡፡