“ኢትዮጵያ እስልምናን ቀድማ የተቀበለች ብቻ ሳትኾን የመሰረተችም ሀገር ናት” ፕሮፌሰር አደም ካሚል

65

ባሕር ዳር: መስከረም 15/2015 ዓ.ም (አሚኮ)ኢትዮጵያ አማኞች ብቻ ሳይኾኑ እምነት እራሱ የሚመርጣት ሀገር ትመስላለች፡፡ ከቀደምቶቹ መካከል ኢትዮጵያ ላይ አሻራውን ያላሳረፈ እምነት እና ሃይማኖት አይገኝም፡፡ የየሃይማኖቶቹ ቅዱሳን መጻሕፍት ኢትዮጵያን ሳይጠቅሱ፣ አበርክቶዎቿን ሳያወሱ እና ሕዝቦቿን ሳያወድሱ አያልፉም፡፡ ከኦርቶዶክስ እስከ ካቶሊክ፤ ከአይሁድ እስከ እስልምና ኢትዮጵያ ስለበጎነት እና ቅድስና ምድራዊ ምሳሌያቸው ነች፡፡

ኢትዮጵያ በክፉ ዘመን መሸሸጊያ፣ በመከራ ዘመን መጠጊያ እና በፍስሃ ዘመን መጸለያ ምድር ናት፡፡ “ደረሳ ረህመት አድርጉልኝ” ብሎ የመጣት፤ ደረሳ በፍቅር እና በእዝነት ቤት ያፈራውን ሁሉ የሚነየትባት ድንቅ ሀገር እንደኾነች ይነገራል፡፡ ኢትዮጵያዊያን እምነታቸውን በተግባር፤ ሃይማኖታቸውን በምግባር የሚገልጡ እውነተኛ አማኞች ተደርገው ይወሰዳሉ፡፡

አንድ ሃይማኖት እና አንድ ቋንቋ ያላቸው በርካታ ሀገራት በእርስ በእረስ ግጭት እና ጦርነት በሚታመሱበት ክፉ ዘመን እንኳን ኢትዮጵያዊያን የሃይማኖት ልዩነት አብሮ የመኖር ደንቀራ ሳይኾንባቸው በፍቅር እና በክብር አብረው የዘለቁ ደግ ሕዝቦች ናቸው፡፡ “እናንተ ኢትዮጵያዊያን ጽናታችሁ እና እምነታችሁ የሚፈተንበት ጊዜ ደርሷል” ተብለው ፈተናን በጽናት፤ መከራን በትጋት ያለፉ ድንቅ ምሳሌዎች ተደርገው ይወሰዳሉ፡፡

ኢትዮጵያ ውስጥ እንኳን ሰዎቹ የሃይማኖት ተቋማቱ ሳይቀር አብረው በጉርብትና ሲኖሩ አንዱ ሌላውን ፈጽሞ አይጎረብጡትም፡፡ ይህ የኢትዮጵያዊያን የአብሮነት እና መቻቻል ጸጋ ከሰዋዊ ባሕሪ የተሻገረ ተፈጥሯዊ ስሪት አለው ያሉን የኢትዮጵያ እና የዓረቡ ዓለም የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት ተመራማሪው ፕሮፌሰር አደም ካሚል ናቸው፡፡ በየትኛውም ወቅት እና ኹኔታ ኢትዮጵያ እና ሃይማኖት ቁርኝታቸው የላቀ፤ ትስስራቸውም የጠበቀ ነው የሚሉት ተመራማሪው ይህ ከቀደምት ነዋሪዎቿ የሥነ-ልቦና ስሪት የመነጨ በጎነት ነው ይላሉ፡፡

እንደ ፕሮፌሰር አደም ዕይታ ጥንታዊቷ ኢትዮጵያ ከእስልምና ሃይማኖት መስፋፋት ጋር የተያያዘ ልዩ ቦታ አላት፡፡ እስልምና ከዓረቡ ዓለም ሀገራት መገፋት እና መከራ ሲደርስበት ከመካ ቀጥላ ሃይማኖቱን የተቀበለች እና ተከታዮቹን ያስተናገደች ተመራጭ ሀገር ናት፡፡ ኢትዮጵያ እስልምናን ስትቀበል ከመዲና እንኳን በሥምንት ዓመት ትቀድማለች፡፡

“ኢትዮጵያ እስልምናን ቀድማ የተቀበለች ብቻ ሳትኾን የመሰረተችም ሀገር ናት” የሚሉት ፕሮፌሰር አደም የነብዩ ሙሐመድን (ሰ.ዐ.ወ) የመውሊድ በዓልን ስናከብር የምናወሳው እና የምናስታውሰው ኢትዮጵያ በነብዩ ዘንድ የነበራትን ክብር እና ፍቅር ነው ይላሉ፡፡ ነብዩ ሙሐመድ (ሰ.ዐ.ወ) ከሰማይ ከተቀበሉት 114 ምዕራፎች ያሉት ቁርዓን ውስጥ ኢትዮጵያ በ23ቱ አንቀጾች ውስጥ በመልካም ስም እና ዝና ትነሳለች፡፡ 30 ቃላት ደግሞ በሐበሾች ቋንቋ ወርደዋል ይላሉ፡፡

የመውሊድ በዓል ኢትዮጵያ በንጉሠ ነገሥቱ ዘመነ መንግሥት የንጉሡ አማካሪ በነበሩት ሼህ ሙሐመድ ሻፊ ጥረት እና ይኹንታ መከበር እንደጀመረ ያነሱት ፕሮፌሰር አደም በደርግ ዘመነ መንግሥት ደግሞ በአዋጅ ከእስልምና ሃይማኖት በዓላት መካከል አንዱ ኾኖ እንዲከበር መወሰኑን ያነሳሉ፡፡ አሁን ላይ መውሊድ የኢትዮጵያ የብዙሃን መገናኛ ድርጅቶች ሰፊ ሽፋን የሚሰጡት ክብረ በዓል ሆኗል፤ ይኽም ታሪካችን ለማስታወስ፣ ክብራችን ለመመለስ እና ትውፊቶቻችንን ለማውረስ ዕድል ይሰጣል ብለውናል፡፡

ዘጋቢ፡- ታዘብ አራጋው

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየባሕር ዳር ከነማ ለመልስ ጨዋታ ወደ ቱኒዝያ ያቀናል፡፡
Next article“በጀት ዓመቱ ከ22 ሺህ በላይ የሥራ ዕድል ለመፍጠር እየሠራሁ ነው” የደብረብርሃን ከተማ አሥተዳደር ሥራ እና ሥልጠና መምሪያ