
ባሕር ዳር: መስከረም 15/2015 ዓ.ም (አሚኮ)ባለፈው ዓመት የኢትዮጵያ ፕሪሜር ሊግ ጠንካራ ፉክክር በማድረግ 2ኛ ደረጃን ይዞ ያጠናቀቀው ባሕር ዳር ከነማ በአህጉራዊ መድረክ ኢትዮጵያን ወክሎ እየተጫወተ ነው፡፡
በአፍሪካ የኮንፌደሬሽን ካፕ ሁለተኛ ዙር የማጣሪያ ውድድር እያካሄደ ያለው ባሕር ዳር ከነማ እግር ኳስ ክለብ ከቱኒዚያው ክለብ አፍሪካ ጋር በአዲስ አበባ አበበ ቢቂላ ስታዲየም ባደረገው የመጀመሪያ ጨዋታ 2 ለ 0 በኾነ ውጤት ማሸነፉ ይታወሳል፡፡
ለደርሶ መልስ ጨዋታው ከነገ ረቡዕ እስከ አርብ ድረስ ወደ ቱኒዝያ የሚያቀናው የባሕር ዳር ከነማ እግር ኳስ ክለብ ልዑክ ከቪዛ እና መሰል ጉዳዮች ጋር የተያያዘ መጉላላት ገጥሞት እንደነበር መዘገባችን ይታወሳል፡፡
የገጠመን የቪዛ መዘግየት ችግር ተፈትቷል ያሉን የክለቡ ሥራ አስኪያጅ ልዑል ፈቃዴ የልዑካን ቡድኑ ከረቡእ እስከ አርብ ድረስ ቱኒዝያ ይገባል ብለዋል፡፡
ባሕር ዳር ከነማ ለመልስ ጨዋታ ወደ ቱኒዝያ ያቀናል ያሉት ሥራ አስኪያጁ በቱኒዚያው የመልስ ጨዋታ የተሻለ ውጤት አስመዝግቦ ወደ ቀጣዩ ዙር ለማለፍ የሚያስችል አካላዊ እና ሥነ-ልቦናዊ ዝግጅት ማድረጉም ተጠቁሟል፡፡
ዘጋቢ፡- ታዘብ አራጋው
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!