
ባሕርዳር፡ መስከረም 15/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የመውሊድ በዓልን ስናከብር የተቸገሩ ወገኖችን በማገዝ፣ በመደጋገፍ፣ ሰላምና አብሮነታችንን በማጠናከር ሊሆን እንደሚገባ የእስልምና ሃይማኖት አባቶች ተናገሩ።
የነብዩ ሙሐመድ 1 ሺህ 498ኛ የመውሊድ በዓል በነገው እለት በተለያዩ መርሃ-ግብሮች የሚከበር ይሆናል።
በአዲስ አበባ ኢዜአ ያነጋገራቸው የእምነቱ አባቶች የመውሊድ በዓል እዝነትን፣ ለጋስነትንና አብሮነትን በተግባር በማሳየት የሚከበር መሆኑን ገልፀዋል።
በመሆኑም የመውሊድ በዓልን ስናከብር የተቸገሩ ወገኖችን በማገዝ፣ በመደጋገፍና ሰላምና አብሮነታችንን በማጠናከር ሊሆን ይገባል ብለዋል።
ከእምነቱ ተከታይ አባቶች መካከል ሸኸ ሙሐመድ ሶቢዩ፤ በዓሉ ሲከበር ነብዩ ሙሐመድ ለሰው ልጆች ያደረጉትን በጎ ተግባር በማስታወስና በመፈጸም እንዲሆን አስገንዝበዋል።
የመውሊድ በዓል የበጎነትና የእዝነት ማሳያ በመሆኑ በተለይም የተቸገሩ ወገኖችን በማገዝና በመደገፍ ሁላችንም አብሮነታችንን በተግባር ማሳየት አለብን ብለዋል።
በመሆኑም በዓሉን ከቤት እስከ ጎረቤት፣ በየአካባቢው የተቸገሩትን በመደገፍ፣ የታመሙትን በመጠየቅና የታረዙትን በማልበስ መሆን እንዳለበት መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።
ሌላኛው አስተያየት ሰጪ ሸኸ መሐመድ ጀማል፤ የመውሊድ በዓልን ስናከብር ለሰው ልጆች ሁሉ መልካም ነገሮችን በማድረግ መሆን አለበት ብለዋል።
የሀገርን ሰላምና አንድነት ለማስጠበቅ ለሚደረገው ጥረት ሁላችንም ደጋፊ እና አጋዥ በመሆን የሰላማችን ዘብ መሆን አለብን ሲሉም ተናግረዋል።
በመሆኑም በዓሉን በአካባቢው የተቸገሩ ወገኖችን በማገዝ ባለን አቅም ሁሉ በመጠየቅ እንዲሆን እንዘጋጅ በማለት ገልፀዋል።
የእምነቱ ተከታዮች በዓሉን ስናከብር ለሀገራችን ሰላም ዱዓ በማድረግ፣ ለተቸገሩ ወገኖች ማዕድ በማጋራትና በፍቅርና በመተዛዘን መሆን አለበት ብለዋል።
በአዲስ አበባ የመውሊድ በዓል በርካታ የእምነቱ ተከታዮችና ኡለማዎች(ሊቃውንቶች) በተገኙበት በታላቁ አንዋር መስጂድ በነገው እለት የሚከበር ይሆናል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!