
ባሕር ዳር: መስከረም 15/2015 ዓ.ም (አሚኮ) 260 ዓመታትን ያስቆጠረ እና በኢትዮጵያ የመጀመሪያው የመውሊድ በዓል የተከበረበት ታሪካዊ ቦታ  ነው። ከደቡብ ወሎ ዞን መቀመጫ ደሴ ከተማ 47 ኪሎ ሜትር ፣ ከአልብኮ ከተማ  ደግሞ 12 ኪሎ ሜትር  ርቀት ላይ ይገኛል – ጀማ ንጉሥ።
በ1756 ዓ.ም በሐጅ ሰዒድ ሙጃሂድ እንደተቆረቆረ የመስጅዱ  ከሊፋ  (አሥተዳዳሪ) ሐጅ ሙሐመድ ኡስማን ነግረውናል፡፡ ሐጅ ሰይድ ሙጃሂድ  በ1735 ዓ.ም በወረባቦ ነበር  የተወለዱት።  በ20 ዓመታቸዉ የሐጅን ቅዱሳዊ  ሥነ ሥርዓት ለማከናወን ወደ መካ  ተጓዙ፤  መካ ላይ አርፈው የሐጅ ሥነ ሥርዓት ካጠናቀቁ በኋላ ወደ ነቢዩ ሙሐመድ (ሰ.ዐ.ወ) መቃብር ቦታ መገኛ  መዲና ከተማ አቀኑ።  መዲና ላይ ለወራት ቆይተው  የሔዱበትን ጉዳይ እንዳጠናቀቁ ወደ ኢትዮጵያ ተመለሱ። ሀገራቸው ከገቡ በኃላም ጀማ  ንጉሥ ሲደርሱ  “የእኛ ቦታ ይቺ ናት” በማለት  ጀማ ንጉሥን ማዕከላቸው አደረጉ።  
ከዚያን ጊዜ ጀምሮ መውሊድ እና ሌሎች ሃይማኖታዊ ክዋኔዎችን ወደ ተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች እንዳስፋፉ አሥተዳዳሪው ነግረውናል። መውሊድም ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ወደ ኢትዮጵያ በመስፋፋት እንዲከበር ተደረገ።
ሐጅ ሰዒድ ሙጃሂድ በቦታው መስጅዱን በመመስረት በርካታ ምሁራንን አስተምረዋል፤ በርካታ ኪታቦችን ጽፈዋል። ከጻፏቸው ኪታቦች መካከል ካሸፈል ኩሩብ፣ ወሲለቱል አስና፣ ሂጀቱን ሷዲቂን፣ አዳቡል ኸልቅ፣ መኡነቱል አልፈቂርና ሪሳለቱል ኢህዋን ይጠቀሳሉ፡፡
ጀማ ንጉሥ በቃል ኪዳን የተመሰረተ መስጂድ በመኾኑ በእስልምና ሃይማኖት ተከታዮች ዘንድ የመውሊድ በዓል በድምቀት ከሚከበርባቸው ቦታዎች ዋነኛው አድርጎታል።
በዓሉ በተከታታይ ለሦስት ቀናት እንደሚከበርም ነው ከሊፋው የገለጹልን።
👉 የመጀመሪያው ቀን ራምሳ የሚባል ሲኾን ዋዜማው ላይ በዱዓ (ጸሎት)፣ በምሥጋናና በዝየራ ይከበራል፡፡
👉 ሁለተኛው አወል በመባል ይታወቃል፡፡ በዓሉ የሚውልበት ቀን ነው፡፡ በዚህ ቀን የተለያዩ ሥርዓቶች በዋናነት ደግሞ የነቢዩ ሙሐመድ (ሰ.ዐ.ወ) መወሊድና ታሪካቸው በስፋት ይዘከርበታል፡፡
👉 ሦስተኛው ደግሞ ሕትሚያ ተብሎ ይጠራል። ምዕመኑ ከአራቱም የሀገሪቱ አቅጣጫ እና ከውጭ ሀገራት ጭምሮ ከቦታው በአንድ ላይ ተሠባስቦ ስለሀገሩ ሰላም ፣ ፍቅር ፣ አንድነት ዱዓ የሚደረግበት እለት ነው። የተጣሉ ሙስሊሞች ካሉም እርቅ ይፈጽሙበታል።
በበዓሉ ላይ ሰዎች ሃይማኖት ፣ ጾታ ፣ እድሜና ሌሎች ቅድመ ኹኔታዎች ሳይገድባቸው በፍቅርና በአንድነት በጋራ ያከብራሉ፡፡
ጀማ ንጉሥ በርካታ የሚዳሰሱ እና የማይዳሰሱ እንደ ልዩ ልዩ ኪታቦች ፣ ድቤ ፣ ረከቦት ፣ ጀበናዎች ፣ መካነ መቃብሮች እና ገድል የተፈጸመባቸው የሰንቦና የወይራ ዛፎች የመሳሰሉ ቅርሶች መገኛ መኾኑን ከደቡብ ወሎ ዞን ባሕልና ቱሪዝም መምሪያ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።
የመምሪያው ኀላፊ መስፍን መኮንን እንዳሉት በዓሉ የቀድሞ ይዘቱን ሳይለቅ እንዲከበር አካባቢውን ለማልማት ትኩረት ተሠጥቶ እየተሠራ ነው ብለዋል።
1ሺህ 498ኛው የመውሊድ በዓል በታላቁ ጀማ ንጉሥ ከመሥከረም 15-17/2016 ዓ.ም ለማክበርም የቅድመ ዝግጅት ሥራው ስለመጠናቀቁም ኀላፊው ገልጸዋል።
በዳግማዊ ተሠራ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
 
             
  
		