“የግሸን ደብረ ከርቤ ንግስ ፣ የመውሊድና የመስቀል በዓላት በሰላም እንዲከበሩ ዝግጅት ተደርጓል” ኮማንድ ፖስቱ

28

ባሕርዳር፡ መስከረም 15/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የግሸን ደብረ ከርቤ ንግስ ፣ የመውሊድና የመስቀል በዓላት በሰላማዊ መንገድ እንዲከበሩ ቅድመ ዝግጅት መደረጉን የደቡብ ወሎ ዞንና የደሴ ከተማ አሥተዳደር ኮማንድ ፖስት አስታውቋል፡፡

የኮማንድ ፖስቱ አባል ሻለቃ ደግሰው ዶሻ እንደገለጹት፤ መስከረም 21 የሚከበረውን የግሸን ደብረ ከረቤ የንግስ በዓል በሰላም እንዲከበር ማኅበረሰቡን በማሳተፍ ተገቢው ቅድመ ዝግጅት ተደርጓል።

ምዕምናኑ እንደከዚህ ቀደሙ ሁሉ ዓመታዊ በዓሉን ያለ ስጋት ማክበር እንደሚችሉ አረጋግጠዋል።

ኅብረተሰቡ ለሰላም ባለው ብርቱ ፍላጎትና ትብብር አካባቢውን ሰላም ማድረግ መቻሉን ጠቅሰው፤ ይህንን ዘላቂ ለማድረግ በቅንጅት እንሰራለን ብለዋል፡፡

የመውሊድ፣ የመስቀልና ደመራ በዓላትም እንዲሁ በሰላም እንዲከበሩ ተገቢውን ስምሪት በመስጠት ቅደመ ዝግጅት መጠናቀቁን አስታውቀዋል።

በዓላቱ በሰላምና በአንድነት እንዲከበሩ የጸጥታ መዋቅሩ ከኅብረተሰቡ ጋር ተቀናጅቶ ቅደመ ዝግጅት አድርጓል ያሉት ሌላው የኮማንድ ፖስቱ አባል ሻለቃ መላኩ ቶላ ናቸው፡፡

ሠራዊቱ የሀገርና የሕዝብን ደህንነት በመጠበቅ የኢትዮጵያ አንድነትና ሰላም ዘላቂ ለማድረግ ማንኛውንም መስዋትነት እየከፈለ መሆኑን ጠቅሰው፤ ኅብረተሰቡም ከሠራዊቱ ጎን በመሰለፍ ሲያደርግ የቆየውን ድጋፍ አጠናክሮ እንዲቀጠል ጠይቀዋል።

የደቡብ ወሎ ዞን የመንግሥት ኮሙኒኬሽን መምሪያ ኃላፊ አቶ እያሱ ዮሐንስ በበኩላቸው፤ የግሸን ደብረ ከርቤ የንግስ በዓልን ለማክበር ወደ ስፍራው የሚመጡ እንግዶችን በተገቢው ለማስተናገድ ዝግጅት መደረጉን ገልጸዋል።

ከኅብረተሰቡና ከሌሎችም ባለድርሻ አካላት ጋር በመቀናጀት ለአንግዶች ምቹ ሁኔታ ለመፍጠር የመንገድ ጠረጋ፣ የውኃ፣ የመብራትና ሌሎችንም አገልግሎት መስጫዎች መመቻቸታቸውን ጠቅሰዋል፡፡

በዓሉን ምክንያት በማድረግ አካባቢውን የቱሪስት መዳረሻ ጭምር በማድረግ ለገቢ ምንጭነት እንዲውልም እየተሠራ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

የትራንስፖርት ችግር እንዳይኖር ከአጎራባች ዞኖችና ከተሞች ጋር በቅንጅት እየተሠራ ነውም ብለዋል።

በግሸን ደብረ ከረቤ የንግስ በዓል ላይ ከአንድ ነጥብ 5 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ ይሳተፋሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ ጠቁመዋል።

በየዓመቱ መስከረም 21 በድምቀት የሚከበረው የግሸን ደብረ ከረቤ የንግስ በዓል በደቡብ ወሎ ዞን አምባሰል ወረዳ ውስጥ መሆኑ ይታወቃል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleለመላው የእስልምና እምነት ተከታዮች በሙሉ እንኳን ለ1498ኛው የመውሊድ በዓል በሠላም አደረሳችሁ።
Next articleየመስቀል ደመራ እና የመውሊድ በዓላት በሰላም እንዲጠናቀቁ በቂ ዝግጅት ማድረጉን የፀጥታና ደኅንነት የጋራ ግብረ-ኃይል ገለፀ።