
ባሕርዳር፡ መስከረም 15/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የፀጥታና ደኅንነት የጋራ ግብረ-ኃይል ለመገናኛ ብዙኃን በላከው መግለጫ፤ ለመላው ሕዝበ ክርሰቲያንና ለመላው ሕዝበ ሙስሊም እንኳን ለመስቀል ደመራና ለመውሊድ በዓላት በሰላም አደረሳችሁ በማለት መልካም ምኞቱን አስተላልፏል።
ሁለቱም በዓላት ሃይማኖታዊ ሥርዓታቸው በሚፈቅደው መሠረት በሰላም ተጀምረው በሰላም እንዲጠናቀቁ ከሃይማኖት አባቶች እና ከሰላም ወዳዱ ኅብረተሰብ ጋር በመተባበር በቂ ዝግጅት አድርጎ ወደ ተግባር መግባቱንም የጋራ ግብረ-ኃይሉ ገልጿል።
በሃይማኖት ሽፋን እኩይ የፖለቲካ አጀንዳዎቻቸውን ለማራመድ የሚደረጉ እንቅስቃሴዎች ተገቢ እንዳልሆነ ሁሉም ተገንዝቦ ከበዓላቱ አከባበር ሥነ-ሥርዓት ውጪ ግጭትና ሁከት ቀስቃሽ መልዕክቶችን በባነር፣ በአልባሳት እንዲሁም እንደ ርችት የመሳሰሉ ተቀጣጣይ ነገሮችን፣ ስለታማና የጦር መሳሪያ በማንኛውም ሁኔታ በዓላቱ ወደ ሚከበሩባቸው ቦታዎች ይዞ መግባት በጥብቅ የተከለከለ መሆኑን የጋራ ግብረ-ኃይሉ ገልጾ፤ ክልከላውን ተላልፈው የበዓላቱን ድባብ ለማደብዘዝ በሚንቀሳቀሱ አካላት ላይ ጥብቅ ሕጋዊ እርምጃ የሚወስድ መሆኑን ከወዲሁ አስታውቋል።
በዓላቱ በሁሉም የሀገራችን አካባቢዎች በሰላም ተጀምረው በሰላም እንዲጠናቀቁ የጋራ ግብረ-ኃይሉ በቂ ዝግጅት አድርጓል። ኅብረተሰቡም ለፀጥታ ኃይሉ አጋዥና ተባባሪ በመሆን የድርሻውን እንዲወጣ አሳስቧል።
በበዓላቱ ድባብ ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ ለመፍጠር የሚደረግ ማንኛውም ሕገ-ወጥ እንቅስቃሴ የሕዝቡን ሰላምና ደኅንነት አደጋ ላይ የሚጥል ስለሆነ የሃይማኖት አባቶች፣ በዓሉን በኮሚቴነት የሚያስተባብሩና የሚመሩ አካላት፣ ሕዝበ ክርስቲያን እና ሕዝበ ሙስሊሙ ከፀጥታ አካላት የሚሰጠውን መመሪያ ከግምት ውስጥ በማስገባት በዓላቱ በሰላም ተጀምረው በሰላም እንዲጠናቀቁ ትብብርና ድጋፍ እንዲያደርጉ የጋራ ግብረ-ኃይሉ ጥሪውን አቅርቧል፡፡
የበዓላቱ ታዳሚዎች የበዓላቱን ሥነ-ሥርዓት የሚያውክ የተለየ እንቅስቃሴ ሲመመለከቱ በአቅራቢያቸው ለሚገኙ የፀጥታ አካላት መረጃ በመስጠት፤ ሰላምና ደኅንነት የማስከበር እንቅስቃሴ ውስጥ ኅብረተሰቡ የጋራ ጥረቱንና አጋርነቱን አጠናክሮ እንዲቀጥል የፀጥታና ደኅንነት የጋራ ግብረ-ኃይል በላከው መግለጫ ጥሪውን እያስተላለፈ፤ ለመላው ሕዝበ ክርስቲያን እንዲሁም ለመላው ሕዝበ ሙስሊም በድጋሚ በዓሉ የሰላም የፍቅር የአንድነትና የደስታ እንዲሆንላቸው ተመኝቷል፡፡
መልካም በዓል!!
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!