
ባሕር ዳር፡- ጥር 17/2012ዓ.ም (አብመድ) ሸንኮራ አገዳው ከፋብሪካው አስቀድሞ በመድረሱ አስወግዶ ዳግም ለማልማት በሚሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ አስፈልጓል፡፡
ለጣና በለስ ስኳር ልማት ፋብሪካ የሚውል የሸንኮራ አገዳ ዳግም ልማት የተጀመረው በ2011 ዓ.ም ነው፡፡ በዚህም 2 ሺህ 3 መቶ ሄክታር መሬት ላይ የተተከለ ሸንኮራ አገዳ ተቆርጦ እንክብካቤ ተደርጎለታል። በ6 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ የተተከለ ሸንኮራ አገዳ ተቆርጦ እንክብካቤ እንዲደረግለትም የመለየት ሥራ ተከናውኗል። ለሥራውም 235 ሚሊዮን ብር ማስፈለጉን ነው የጣና በለስ ስኳር ልማት ኘሮጀክት ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ አንተነህ አሰጌ የተናገሩት፡፡ ሥራ አስኪያጁ እንደገለጹት በስኳር ኮርፖሬሽን ሥራ አመራር ቦርድ የተፈቀደው ግን ለሥራው ከሚያስፈልገው 215 ሚሊዮን ብር ብቻ ነው።
ሸንኮራ አገዳው የሚቆረጠው ፋብሪካው ሥራ ከመጀመሩ በፊት ለጥቅም በመድረሱ እና በማርጀቱ ነው፡፡ ፋብሪካው ባይጓተት ኖሮ ጥቅም ላይ ይውል ነበር፡፡ ይህም በሚሊዮን የሚቆጠር ሀብት እንዲባክን እያደረገ ነው፡፡
ለሥኳር ፋብሪካው ጥቅም ላይ እንዲውል ታስቦ እየለማ ያለው የሸንኮራ አገዳ ባለፈው ኅዳር ተወግዶ በአዲስ መልኩ እንክብካቤ ሊደረግለት ይገባ ነበር፡፡ ይሁን እንጂ ሥራው አልተጀመረም፡፡ በመሆኑም ሥራው ዘግይቶ የካቲት ላይ ሊጀመር እንደሚችል ነው የተገለጸው፡፡
ጣና በለስ ቁጥር አንድ ስኳር ፋብሪካ የሙከራ ምርቱን ይጀምራል በተባለበት የፊታችን ግንቦት ላይ የሸንኮራ አገዳ ምርቱ እንዲደርስ ጥረት እንደሚደረግም አቶ አንተነህ አስታውቀዋል፡፡
ከ2005 ዓ.ም ጀምሮ 13 ሺህ 1 መቶ 47 ሄክታር መሬት ላይ ሸንኮራ አገዳ መተከሉን ከጣና በለስ ስኳር ልማት ኘሮጀክት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።
የጣና በለስ የተቀናጀ የሥኳር ልማት ፕሮጀክት በአማራ ክልል አዊ ዞን ጃዊ ወረዳ ነው እየተገነባ ያለው፡፡ፕሮጀክቱ በ40 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ የሚለማ ሸንኮራ አገዳ በግብዓትነት እንደሚጠቀም ይጠበቃል፡፡ በመጪው ግንቦት ወደ ሙከራ ምርት ይገባል የተባለውን ጨምሮ ፋብሪካዎቹ ወደ ሙሉ ምርት ሲገቡ እያንዳንዳቸው በዓመት 2 ሚሊየን 420 ሺህ ኩንታል ሥኳር እና 20 ሚሊየን 827 ሺህ ሊትር ኢታኖል የማምረት አቅም ይኖራቸዋል ተብሎ ይጠበቃል።
የፋብሪካው የግንባታ ሂደት በፌዴራል ተቋማት የሥራ ኃላፊዎች፣ ባለሙያዎችና ጋዜጠኞች እየተጎበኘ ነው።
ዘጋቢ፡- ኪሩቤል ተሾመ
