የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ከክለቦች ጋር በቅንጅት መሥራት እንደሚገባው ተጠቆመ።

73

ባሕር ዳር: መስከረም 15/2015 ዓ.ም (አሚኮ)የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የእግር ኳሱን ውጤታማነት ለማረጋገጥ ከክለቦች ጋር በቅንጅት መሥራት እንዳለበት በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የጤና፣ ማኅበራዊ ልማት፣ ባሕልና ስፖርት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አሳሰበ።

ቋሚ ኮሚቴው ከኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽን የሥራ ኀላፊዎችና ሥራ አስፈጻሚ አባላት ጋር በእግር ኳሱ ዕድገት ተግዳሮቶችና በፌዴሬሽኑ አሠራር ዙሪያ ውይይት አድርጓል።

በዚሁ በፌዴሬሽኑ ጽሕፈት ቤት በተከናወነው የመስክ ምልከታ ወቅት የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ ወርቅሰሙ ማሞ እንዳሉት የሀገራችን ሕዝቦች ለእግር ኳሱ ካላቸው ልዩ አድናቆትና ፍቅር ተገቢ ውጤት ለማምጣት ፌዴሬሽኑ በክለቦች ውጤታማነት ላይ አተኩሮ ሊሠራ ይገባል ብለዋል። ቋሚ ኮሚቴው ለእግር ኳሱ ውጤት መሻሻል ተገቢውን ድጋፍ እንደሚያደርግም ሰብሳቢዋ ተናግረዋል።

የቋሚ ኮሚቴው ምክትል ሰብሳቢከይረዲን ተዘራ (ዶ.ር) የአፍሪካ የእግር ኳስ ማኅበር መስራች ለኾነችው ኢትዮጵያ የሚመጥን የእግር ኳስ ውጤት ለማምጣት ከታች ጀምሮ ከክለቦች ጋር በመቀናጀት መሠራት አለበት ብለዋል።

በእግር ኳሱ ዙሪያ እየገጠሙ ያሉ ችግሮችን ለመፍታት በጥናት ላይ የተመሰረተ መፍትሔ መተግበር እንዳለበትም አስገንዝበዋል።

የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዘዳንት ኢሳያስ ጅራ ፌዴሬሽኑ የሀገሪቱን እግር ኳስ ውጤት ለማሻሻል በልዩ ትኩረት እየሠራ መኾኑን ገልጸዋል። የበጀት እጥረት፣ የክለቦች ተተኪ ለማፍራት አቅደው አለመሥራት፣ ትውልደ ኢትዮጵያዊያንን ከውጭ ሀገራት አምጥቶ ለማጫወት ያሉ የሕግ ክፍተቶች፣ ከተለያዩ አካላት ለእግር ኳሱ የሚሰጡ ትኩረቶች ማነስ እና ደረጃውን የጠበቀ ስቴዲየም ያለመኖር የኳሱን እድገትና ውጤት እንደጎዳው ተናግረዋል።

የቋሚ ኮሚቴው አመራርና አባላት ፌዴሬሽኑ በፈተና ውስጥም ኾኖ የሀገር ውስጥና አህጉራዊ ውድድሮችን ለማከናወን እያደረገ ያለው ተግባር ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበትም ገልጸዋል። በዘርፉ ያለውን ችግር ለመፍታት የባሕልና ስፖርት ሚኒስቴርና ፌደሬሽኑ ተቀራርበው መሥራት እንዳለባቸውም አሳስበዋል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“የገጠመንን መጉላላት ፈትተን ለመልሱ ጨዋታ በአሰብነው ጊዜ ቱኒዚያ ደርሰን ለጨዋታው እንዘጋጃለን።” የባሕር ዳር ከነማ ክለብ ሥራ አስኪያጅ
Next article“እንኳን ለመውሊድ በዓል አደረሳችሁ” ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር)