“የገጠመንን መጉላላት ፈትተን ለመልሱ ጨዋታ በአሰብነው ጊዜ ቱኒዚያ ደርሰን ለጨዋታው እንዘጋጃለን።” የባሕር ዳር ከነማ ክለብ ሥራ አስኪያጅ

32

ባሕር ዳር: መስከረም 15/2015 ዓ.ም (አሚኮ)የገጠማቸውን መጉላላት ቶሎ በመፍታት ለመልሱ ጨዋታ በታሰበው ጊዜ ቱኒዚያ በመገኘት ለጨዋታው እንደሚዘጋጁ የባሕርዳር ከነማ እግርኳስ ክለብ ሥራ አስኪያጅ ልዑል ፈቃዴ ገልጸዋል።

በአፍሪካ ኮንፌዴሬሽን ዋንጫ እየተሳተፈ የሚገኘው ባሕር ዳር ከነማ ከቱኒዚያው ክለብ አፍሪካ ጋር ተደልድሎ የመጀመሪያ ጨዋታውን አዲስ አበባ ላይ 2 ለ 0 ማሸነፉ ይታወሳል።

የመልሱ ጨዋታ ደግሞ እሁድ መስከረም 20 በቱኒዚያ ሊካሄድ ከቀጠሮ ተይዞለታል።ለዚህ ጨዋታ የጣና ሞገዶቹ መስከረም 16 እና 17 ወደ ቱኒዚያ ለመብረር ቢዘጋጁም የቪዛ ጉዳይ አለመጠናቀቁን ነው የክለቡ ሥራ አስኪያጅ ልዑል ፈቃዴ የተናገሩት።

አስፈላጊው ሁሉ መረጃ በኢትዮጵያ ለቱኒዚያ ኢምባሲ ባለፈው ሳምንት ማቅረባቸውንም ገልጸዋል። ለመስከረም 14 ቪዛው ተጠናቅቆ እንደሚደርሰን ኢምባሲው ቃል የገባ ቢኾንም በተጠቀሰው ጊዜ አልደረሰልንም ብለዋል አቶ ልዑል።

የቱኒዚያ ኢምባሲ በሰው ኀይል እጥረት ምክንያት በተባለው ጊዜ ቪዛውን አለማድረሱን ገልጾልናል ነው ያሉት ሥራ አስኪያጁ።

ከኢምባሲው ጋር በተደረገ ውይይት ዛሬ ረፋድ ድረስ 26 ቪዛዎችን ሠርተው አሰረክበውናል ፤ ቀሪውንም ዛሬ ለማስጨረስ በኢትዮጵያ ከቱኒዚያ ኢምባሲ ፣ ከኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን እና ከአፍሪካ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ጋር እየተነጋገር ነው፣ተስፋም አለን ብለዋል አቶ ልዑል።

የገጠመንን መጉላላት ቶሎ ፈተን በአሰብነው ጊዜ ቱኒዚያ ደርሰን ለጨዋታው እንዘጋጃለን ሲሉም ሃሳባቸውን ለአሚኮ ገልጸዋል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“ከበዓላት ጋር ተያይዞ ከሚሰራጩ ሐሰተኛ የገንዘብ ኖቶች ተጠንቀቁ” የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ
Next articleየኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ከክለቦች ጋር በቅንጅት መሥራት እንደሚገባው ተጠቆመ።