
ባሕርዳር፡ መስከረም 15/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በቀጣዮቹ ቀናት ከሚከበሩ የመውሊድ፣ የመስቀል፣ የኢሬቻ እና ሌሎች በዓላት ጋር ተያይዞ ከሚሰራጩ ሐሰተኛ የገንዘብ ኖቶች ኅብረተሰቡ ጥንቃቄ እንዲያደርግ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ አሳስቧል።
በዓላቱን እንደ አጋጣሚ በመጠቀም ወንጀለኞች በቻሉት መንገድ ሁሉ ሐሰተኛ ገንዘቦችን በማሳተም እና በማሰራጨት በበዓላት ወቅት ግብይት ላይ ለማዋል ጥረት በማድረግ ላይ መሆናቸውን መረጃዎች እንደደረሱት ባንኩ ገልጿል።
በመሆኑም፣ ኅብረተሰቡ በግብይት ወቅት በሐሰተኛ ገንዘቦች ክፍያ ምክንያት ሊያጋጥም ከሚችል ያልታሰበ ጉዳት ራሱን እንዲጠብቅ አሳስቧል።
“በሁሉም ገንዘቦች ላይ የሚገኙ የደኅንነት መጠበቂያ ምልክቶችን በትኩረት በመመልከት፣ ለግብይት በሚቀርቡላችሁ ገንዘቦች ላይ ከሚታዩ ምልክቶች ጋር በማነፃፀር ሕገ-ወጦች ከሚያዘዋውሩት ሐሰተኛ ገንዘቦች ራሳችሁን እንድትጠብቁ በአጽንኦት እናሳስባለን” ብሏል ባንኩ ባወጣው መግለጫ።
ከዚሁ ጋር ሐሰተኛ ገንዘቦችን የሚያትሙ፣ የሚያዘዋውሩ እና ለመገበያየት የሚያቀርቡ ወንጀለኞችን በአካባቢው ለሚገኙ የፀጥታ አካላት ወዲያውኑ በመጠቆም ወንጀሉን ለመከላከል ኅብረተሰቡ የበኩሉን አስተዋፅኦ እንዲያደርግ ባንኩ ጥሪ አቅርቧል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!