ገዳዩ ኮሮና ቫይረስ በ 12 ሀገራት መሥፋፋቱ ሥጋት ፈጥሯል፡፡

312

ባሕር ዳር፡- ጥር 17/2012ዓ.ም (አብመድ) ኮሮና ቫይረስ በቻይና 56 ሰዎችን ለሞት፣ 2 ሺህ ሰዎችን ደግሞ ለህመም ዳርጓል፡፡

የኮሮና ቫይረስ ከቀላል እስከ ከባድ የመተንፈሻ አካል ሕመም የሚያስከትልና ለሞትም ሊዳርግ የሚችል የቫይረስ ዝርያ ነው፡፡ በሽታው በትንፋሽ፣ ባልበሰሉ ምግቦች እና በቫይረሱ ከታመሙ ሰዎች ጋር በሚደረግ ንክኪ ይተላለፋል። ትኩሳት፣ ሳል እና የአተነፋፈስ ችግር ደግሞ ምልክቶቹ ናቸው፡፡ ቫይረሱ ከቻይና ባሻገር በአሜሪካ፣ ፈረንሳይ፣ አውስትራሊያ፣ ታይላንድ፣ ጃፓን፣ ደቡብ ኮሪያ፣ ታይዋን፣ ቬትናም፣ ሲንጋፖር፣ ማሌዥያ እና በኔፓል እንደተከሰተ እየተዘገበ ነው፡፡ በሽታው በሀገራቱ የተከሰተው ደግሞ በሥራ እና በሌሎች ምክንቶች ከቻይናዋ ውሃን ቆይተው ወደ ሀገራቸው በገቡ ሰዎች አማካኝነት እንደሆነ ተገልጧል፡፡

ቫይረሱ በቻይናዋ ውሃን ከተማ ከተከሰተ ጀምሮ ቢያንስ የ56 ሰዎች ህይወት አልፏል፤ 2 ሺህ ሰዎች ደግሞ በቫይረሱ መጠቃታቸው ታውቋል፡፡ የቻይናው ፕሬዝዳንት ሽ ጅንፒንግ ዜጎች ከፍተኛ ጥንቃቄ እንዲያደርጉ አሳስበዋል፡፡ ፕሬዝዳንቱ ለሀገሪቱ ከፍተኛ ባለስልጣናት እንደተናገሩት ሀገሪቱ ‹‹ከባድ ፈተና›› አጋጥሟታል፡፡

የቫይረሱ ስርጭት መስፋፋቱን ተከትሎ አሜሪካ በውሃን ከተማ የሚገኙ የቆንስላ ሰራተኞቿ የፊታችን ማክሰኞ ለቅቀው እንዲወጡ አዝዛለች፡፡፡

ቫይረሱ በተከሰተባት ውሃን ግዛት 1 ሺህ 300 አዲስ በቫይረሱ የተጠቁ ህሙማን የሚታከሙበት ተጨማሪ የድንገተኛ ህክምና መስጫ ሆስፒታል ግንባታ በሳምንቱ ውስጥ አንዲጀመር እና በወሩ አጋማሽ ተጠናቅቆ አገልግሎት እንዲሰጥ ታስቦ እየተሠራ ነው፡፡ 1 ሺህ አልጋዎች ያሉት የድንገተኛ ህሙማን አገልግሎት መስጫ ሆስፒታል በቫይረሱ ለተያዙት ሰዎች አገልግሎት እየሰጠ መሆኑ ይታወሳል፡፡

የቫይረሱ መነሻ የሆነችው ውሃን ግዛት ወደ ምትገኝበት ሁቤ ግዛት ደግሞ ልዩ ወታደራዊ የህክምና ቡድን እንደተላከ ታውቋል፡፡ ቫይረሱ ታህሳስ ላይ ከተከሰተ ጀምሮ በቻይናም ሆነ በሌሎች አካባቢዎች ልዩ ትኩረት እየተሰጠው እንደሆነም ተነግሯል፡፡

ምንጭ፡- አልጀዚራ እና ቢቢሲ

ዘጋቢ፡- ዳግማዊ ተሰራ

Previous articleበሰዎች ግድያ እና ማፈናቀል የተጠረጠሩ 13 ግለሰቦች በቁጥጥር ሥር ዋሉ
Next articleጣና በለስ ቁጥር አንድ የሥኳር ፋብሪካ ግንባታን ግንቦት ላይ ለማጠናቀቅ እየተሠራ ነው።