
ባሕር ዳር: መስከረም 15/2015 ዓ.ም (አሚኮ)በአማራ ክልል የሩዝ ልማትን ለማስፋፋት በተደረገው ጥረት በሩዝ የሚለማው መሬትና የሚገኘው ምርት እየጨመረ መምጣቱን የክልሉ ግብርና ቢሮ አስታወቀ።
በክልሉ በ2015/2016 የምርት ዘመን በሩዝ ሰብል ከሚለማው መሬት 5 ነጥብ 4 ሚሊዮን ኩንታል ምርት እንደሚጠበቅ ቢሮው ገልጿል።
በቢሮው የሩዝ ሰብል ልማት አስተባባሪ ወይዘሮ እንዬ አሰፋ እንደገለጹት ምርቱ የሚጠበቀው የሩዝ ልማቱ በሚካሔድባቸው ሩዝ አብቃይ 17 ወረዳዎች ውስጥ ከለማው 83 ሺህ 650 ሄክታር መሬት ላይ መኾኑን ገልጸዋል።
ክንውኑ ካለፈው ተመሳሳይ የምርት ዘመን ጋር ሲነፃፀር በ22 ሺህ ሄክታር እና በምርት ደግሞ ከ2 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ብልጫ እንደሚኖረው አመልክተዋል።
ይህም በሩዝ የሚለማው መሬትና የሚገኘው ምርት እየጨመረ መምጣቱን ያመለክታል ብለዋል። የፎገራ ብሔራዊ የሩዝ ምርምርና ሥልጠና ማዕከልና ሌሎች ድርጅቶች በሚያቀርቡት የተሻሻለ ዝርያ አርሶ አደሩ የምግብ ዋስትናውን እንዲያረጋጥና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነቱንም እንዲያሳድግ ማገዙን ተናግረዋል።
በደቡብ ጎንደር ዞን ፎገራ ወረዳ የአጓኮኪት ቀበሌ አርሶ አደር ፀሐይነው ስንሻው በሰጡት አስተያየት፤ ሁለት ሄክታር የሚጠጋ መሬት በሩዝ ሰብል እያለሙ መኾናቸውን ገልጸዋል።
ዘንድሮ የማዳበሪያ እጥረት ቢያጋጥምም እየለማ ካለው የሩዝ ሰብል እስከ 130 ኩንታል ምርት አገኛለሁ ብለው እንደሚጠብቁ ተናግረዋል።
የተሻለ ምርት የሚሰጡ የሩዝ ዝርያዎች በየጊዜው መቅረባቸው የተሻለ ተጠቃሚ እንድንሆን አስችሎናል ያሉት ደግሞ የዚሁ ወረዳ አርሶ አደር አለባቸው ጓዴ ናቸው።
በመኸሩ ወቅት ከአንድ ሄክታር ተኩል በሚበልጥ መሬት ላይ ሩዝ እያለሙ እንደሚገኙም ገልጸዋል።
ኢዜአ እንደዘገበው ባለፈው ዓመት በክልሉ በሩዝ ሰብል ከለማው 61 ሺህ 497 ሄክታር መሬት ከ3 ነጥብ 2 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት መገኘቱን የግብርና ቢሮው አስታውቋል።
በአማራ ክልል ለሩዝ ሰብል ልማት ተስማሚ የኾነ ከአንድ ሚሊዮን ሄክታር በላይ መሬት መኖሩም ከቢሮው የተገኘው መረጃ ያመለክታል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!