
ባሕርዳር፡ መስከረም 15/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የአዲስ አበባ ከተማ ከፍተኛ አመራሮች እና የሃይማኖት አባቶች የመስቀል በዓልን በመስቀል አደባባይ ለማክበር ያለመ የማጽዳት ሥራ አካሂደዋል።
በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የአዲስ አበባ አሥተዳደር ከተማ ዋና ሥራ አሥኪያጅ ጥራቱ በየነ፣ የሰላምና ጸጥታ ቢሮ ኅላፊዋ ሊዲያ ግርማ ፣ የሃይማኖት አባቶች እና የከተማዋ ነዋሪዎች መስቀል አደባባይን ለመስቀል በዓል በማፅዳት መርሐ ግብር ላይ ተሳትፈዋል ።
ከተለያዩ የሃይማኖት ተቋማት የተገኙ አባቶች የመስቀል በዓል በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርሥቲያን ከሚከበሩ ታላላቅ በዓላት መካከል ልዩ ድርሻ ያለው ነው ብለዋል።
ከየሃይማኖት ተቋማቱ በጽዳት መርሐ ግብሩ ላይ የተገኙት አባቶች የእንኳን አደረሳችሁ እና የመልካም ምኞት መልእክታቸውን እንዲሁም አብሮነታቸውን ገልጸዋል።
በዓሉ ኢትዮጵያዊ አብሮነታችንን እና ሰላማችን የምናጠናክርበት መኾን እንዳለበትም ጠቁመዋል።
በመድረኩ በመገኘት የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት ሊቀ አዕላፍ ቀሲስ በላይ መኮንን መስቀል የብርሃን ምልክት ነው፤ ችቦ እና ደመራ ተቃጥለው ብርሃን እንደሚሰጡ ሁሉ እኛም ሰዎች አንዳችን ከሌላው ጋር በጋራ መቆም እና ዋጋ መክፈል እንዳለብን እንማራለን ብለዋል።
በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የአዲስ አበባ ከተማ ዋና ሥራ አሥኪያጅ ጥራቱ በየነ ዘንድሮ የመስቀል በዓል እና የመውሊድ በዓል በአንድ ቀን መከበራቸው ልዩ ኹነት ያደርገዋል ብለዋል። በዓላቱ አብሮነታችንን እና ወንድማማችነታችንን የምንገልጽባቸው ናቸውም ብለዋል።
በዓላቱ በሰላም ተከብረው እንዲጠናቀቁ ሁሉም የእምነት ተከታዮች እና ወጣቶች እንደወትሮው ሁሉ ለሰላም ዘብ መቆም ይገባቸዋል ሲሉም ተናግረዋል።
የመስቀል በዓል እና የመውሊድ በዓል በኢትዮጵያዊ አንድነት እና በአብሮነት እንዲከበርም መልእክታቸውን አስተላልፈዋል ።
ዘጋቢ:- አየለ መስፍን
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!