
ባሕር ዳር: መስከረም 14/2015 ዓ.ም (አሚኮ)1498ኛው የነቢዩ ሙሐመድ (ሰ.ዐ.ወ) የልደት በዓል (መውሊድ) የፊታችን መስከረም 16/2016 ዓ.ም ይከበራል፡፡ የአማራ ክልል እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ሼህ ጀውሐር ሙሐመድ መልካም ምኞታቸውን አስተላልፈዋል፡፡
ነብዩ ሙሐመድ (ሰ.ዐ.ወ) ስለ ሰላም፣ እኩልነት፣ መከባበር፣ መረዳዳት፣ ፍትሕ እና ስለ ሀቀኝነት ማስተማራቸውን ተናግረዋል። የእምነቱ ተከታዮችም ይህንን የነቢዩን አስተምህሮ ተግባራዊ ማድረግ ይገባል ብለዋል፡፡ በተለይም ደግሞ በዓሉን ስናከብር በመረዳዳት እና በመተሳሰብ ሊኾን ይገባል ብለዋል፡፡
እስልምና ሰላም መኾኑን ያነሱት ፕሬዚዳንቱ የሃይማኖቱ ተከታይ በዓሉን ሰላማዊ በኾነ መንገድ ሊያከብር ይገባል ብለዋል፡፡
በመውሊድ የሚሰበሰብ ሁሉ ለሀገሩ ሰላም፣ አንድነት እና ፍቅር ዱዓ ማድርግ እንደሚገባም ጠይቀዋል፡፡ ለመላው የእስልምና እምነት ተከታዮችም መልካም ምኞታቸውን ገልጸዋል።
ዘጋቢ፡-ዳግማዊ ተሠራ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!