በደብረ ብርሃን ከተማ አሥተዳደር ስር የሚገኙ 81 ትምህርት ቤቶች የመማር ማስተማር ሥራ ዛሬ ጀመሩ።

57

ደብረ ብርሃን፡ መስከረም 14/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በደብረ ብርሃን ከተማ አሥተዳደር ስር በሚገኙ ሁሉም የግል እና የመንግሥት ትምህርት ቤቶች የመማር ማስተማር ሥራ ዛሬ ተጀምሯል። በከተማ አሥተዳደሩ ከቅድመ መደበኛ እስከ አጠቃላይ ሁለተኛና መሰናዶ ያሉ 81 ትምህርት ቤቶች ናቸው ሥራቸውን የጀመሩት። በ2016 የትምህርት ዘመን ከ40 ሺህ በላይ ተማሪዎችን ለማስተማር ምዝገባው ቀደም ብሎ ተጠናቅቋል።

የከተማ አሥተዳደሩ ትምህርት መምሪያ ኀላፊ መቅደስ ብዙነህ እዳሉት የትምህርት ዘመኑ የተሳካ ሥራ እንዲከናወንበት ለማስቻል በቁርጠኝነት እየተንቀሳቀሱ ነው። አሁንም ደረጃቸውን ያላሟሉ ትምህርት ቤቶች ስላሉ በተሻለ መልኩ ለመገንባት ባለድርሻ አካላት የበኩላቸውን ሚና እንዲጫወቱም መምሪያ ኀላፊዋ መልእክት አስተላልፈዋል።

የደብረብርሃን ከተማ አሥተዳደር ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት የፖለቲካ ዘርፍ ኀላፊ ታጠቅ ገድለአማኑኤል በትምህርት አጀማመር ሥነ ሥርዓቱ ተገኝተው ለተማሪዎች መልእክት አስተላልፈዋል። ተማሪዎች ለየደረጃቸው የሚመጥን ዕውቀትን ከሥነ ምግባር ጋር እንዲቀስሙ መክረዋል። ለዚህም በመንግሥት ደረጃ በቂ ዝግጅት ተደርጓል ነው ያሉት። ባለድርሻ አካላት ሚናቸውን እንዲወጡም መልእክት አስተላልፈዋል።

በደብረብርሃን ከተማ ከሚገኙ አንጋፋ ትምህርት ቤቶች መካከል አንድነት የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት ይጠቀሳል። ትምህርት ቤቱ 1 ሺህ 610 ተማሪዎችን በአግበቡ ለማስተማር ሙሉ ዝግጅት አድርጓል። መንግሥታዊና መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማትን በማስተባበርም የትምህርት ቁሳቁስ አንዲሟላ እና ጥራትን የሚያረጋግጡ አዳዲስ አሠራሮች እንዲተገበሩ የተሻለ ሥራ ሠርቷል ነው የተባለው።

ዘጋቢ:- ደጀኔ በቀለ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየደሴ ከተማ የ2016 ዓ.ም የትምህርት ዘመን ከ54ሺ በላይ ተማሪዎችን በይፋ ማስተማር ጀመረ።
Next articleለመውሊድ በዓል የሚሰባሰብ ሁሉ የነቢዩ ሙሐመድን (ሰ.ዐ.ወ) አስተምህሮ ተግባራዊ ማድረግ እንደሚገባ የአማራ ክልል እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት አሳሰበ፡፡