
ባሕር ዳር፡- ጥር 17/2012ዓ.ም (አብመድ) በቤኔሻንጉል ጉሙዝ ክልል መተከል ዞን ወምበራ ወረዳ ሰዎችን በመግደል እና በማፈናቀል የተጠረጠሩ ግለሰቦች መያዛቸውን የክልሉ የሰላም ግንባታ እና ጸጥታ ቢሮ ገልጧል፡፡
ባለፈው ጥር 8/2012 ዓ.ም በቤኔሻንጉል ጉሙዝ ክልል መተከል ዞን ወምበራ ወረዳ ኮንግ ቀበሌ በሰላማዊ ዜጎች ላይ ጥቃት መፈጸሙን መዘገባችን ይታወሳል፡፡ በጥቃቱም የሰዎች ሕይወት አልፏል፤ ንብረት ወድሟል፤ ብዙዎችም ተፈናቅለዋል፡፡
በድርጊቱ የተጠረጠሩ ሰዎች በአካባቢው ማኅበረሰብ ጥቆማ፣ በፌዴራል ፖሊስ እና በመከላከያ ሠራዊት አባላት ክትትል ትናንት ጥር 16/2012 ዓ.ም እንደተያዙ የልልሉ የሰላም ግንባታ እና ጸጥታ ቢሮ ኃላፊ አቶ አበራ ባዬታ በተለይ ለአብመድ ገልጸዋል፡፡
በቁጥጥር ሥር የዋሉት 13 ግለሰቦች ናቸው፤ ከእነዚህ ውስጥ ሁለቱ በግድያ፣ ቀሪዎቹ ደግሞ ንብረት በመዝረፍ የተጠረጠሩ ናቸው ብለዋል አቶ አበራ፡፡
በግድያ ከተጠረጠሩት ውስጥ አንደኛው ከአንድ የእጅ ቦምብ ጋር እንደተያዘም ነው ያስታወቁት፡፡ እንደ ቢሮ ኃላፊው መረጃ ቀሪ ዘጠኝ ተጠርጣሪዎችን ለመያዝ የፀጥታ አካላትና የአካባቢው ማኅበረሰብ በጋራ እየሠሩ ነው፡፡
አሁን ላይ የመከላከያ ሠራዊት አባላት፣ የፌዴራል ፖሊስ፣ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች እና የአካባቢው የጸጥታ አካላት ሕዝቡን እያረጋጉ እንደሆነና ከተጎጅዎች ጋርም ውይይት እየተደረገ መሆኑን አቶ አበራ ተናግረዋል፡፡