“በአዲሱ የትምህርት ዘመን የተሻለ ውጤት ለማምጣት ተዘጋጅተናል”ተማሪዎች

40

ባሕር ዳር: መስከረም 14/2015 ዓ.ም (አሚኮ)በአማራ ክልል የ2016 ዓ.ም የትምህርት ዘመን መደበኛ መማር ማስተማር ሥራ ተጀምሯል። በባሕርዳር ከተማ አሥተዳደር በአዲሱ ዓመት ተማሪዎች ትምህርታቸውን ጀምረዋል። ከእረፍት በኋላ በወቅቱ ወደ ትምህርት ቤት የመጡ ተማሪዎች ደስተኞች መኾናቸውን ተናግረዋል። መምህራንም ለማስተማር ቅድመ ዝግጅት አድርገው ማስተማር መጀመራቸውን ገልጸዋል።

በጣና ሐይቅ አጠቃላይ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት መምህርት ጽላተ ሙሴ የዓመቱን የመጀመሪያ የመማር ማስተማር ሥራ መጀመራቸውን ተናግረዋል። ተማሪዎችን በተቻለ መጠን ለማብቃት ጥረት እንደሚያደርጉም አስታውቀዋል። ተማሪዎች ዝግጁ እንዲኾኑ አስቀድመው መሥራታቸውንም አስረድተዋል። ተወዳዳሪ የኾኑ ተማሪዎችን ለማፍራትም ጥረት እንደሚያደርጉም አስታውቀዋል።

የ10ኛ ክፍል ተማሪዋ ጽዮን ሙሉዬ ቀድሞ ትምህርት መጀመሩ በጊዜ ለመጨረስና ለመዘጋጀት ጥሩ አጋጣሚ መኾኑን ተናግራለች። መምህራንም ለመማር ማስተማር ዝግጁ ኾነው ማስተማር ጀምረዋል ብላለች። አዲሱን ሥርዓተ ትምህርት ለመማርና ውጤታማ ለመኾን መዘጋጀቷንም ነግራናለች።

የ10ኛ ክፍል ተማሪ ፍርኑስ ሞገስ ትምህርት በጊዜው መጀመሩ ውጤታማ ለመኾን እንደሚያግዛቸው ገልጻለች። የትምህርት ሥርዓቱ አጀማመርም መልካም መኾኑን ተናግራለች። በአዲሱ ዓመት የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ በመምህራን እገዛ እንደሚጥሩም ገልጻለች።

ሌላው የ10ኛ ክፍል ተማሪ ያሬድ ምህረት እንደነገረን ደግሞ መምህራን ስለ አዲሱ ሥርዓተ ትምህርት ገለጻ እንዳደረጉላቸው ገልጿል። ከባለፈው የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ የሥነ ልቦና ዝግጅት ማድረጉንም ተናግሯል። ተማሪዎች ወደ ትምህርት ቤት በመምጣት ትምህርታቸውን መከታተል እንደሚገባቸውም ገልጿል።

የጣና ሐይቅ አጠቃላይ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ርእሰ መምህር ሙጬ ባዘዘው የትምህርት ቅድመ ዝግጅት ሲያደርጉ ቆይተው በወጣው እቅድ መሠረት ትምህርት መጀመራቸውን ገልጸዋል። አዲሱን ሥርዓተ ትምህርት የማስተዋወቅ እና የማስተማር ሥራ እየተሠራ መኾኑንም ተናግረዋል። ትምህርት ቤቱን ሳቢና ማራኪ ለማድረግ የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች መሠራታቸውንም አስታውሰዋል። ቤተ ሙከራዎችን ዘመናዊ ለማድረግ መሥራታቸውንም ገልጸዋል። የአዲሱ ሥርዓተ ትምህርት መጽሐፍት መዘግየት እንደገጠማቸው ያነሱት ርእሰ መምህሩ መጽሐፍቱ እስኪደርሱ ሌሎች አማራጮችን እየወሰዱ መኾናቸውንም ተናግረዋል። በአዲሱ ዓመት ተማሪዎች የተሻለ ውጤት እንዲያመጡ በትኩርት እንደሚሠሩም ገልጸዋል። በተለይም የሀገር አቀፍ ፈተና ተፈታኞች ተወዳደሪ እንዲኾኑ ለማድረግ የእስካሁኖቹን ተሞክሮዎች በመውሰድ እንደሚሠሩም ተናግረዋል። የተማሪዎች ሥነ ምግባር ትኩረት ይሰጠዋልም ብለዋል። አቅም ለሌላቸው ተማሪዎች የመማሪያ ቁሳቁስ እየሠጡ መኾናቸውንም ተናግረዋል።

የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ እና የባሕርዳር ከተማ አሥተዳደር ትምህርት መምሪያ የሥራ ኀላፊዎች የዓመቱን የትምህርት ማስጀመሪያ ቀን በትምህርት ቤቶች ተዘዋውረው ተመልክተዋል።

ዘጋቢ:- ታርቆ ክንዴ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article” 2 ነጥብ 7 ሚሊዮን ተማሪዎች ተመዝግበዋል፣ የዓመቱ መደበኛ ትምህርትም ተጀምሯል” የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ
Next articleበደብረ ብርሃን ከተማ የ2016 ዓ.ም ትምህርት በሁሉም ትምህርት ቤቶች ተጀመረ።