” 2 ነጥብ 7 ሚሊዮን ተማሪዎች ተመዝግበዋል፣ የዓመቱ መደበኛ ትምህርትም ተጀምሯል” የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ

43

ባሕርዳር፡ መስከረም 14/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል የ2016 ዓ.ም መደበኛ ትምህርት ተጀምሯል። የዓመቱን የመጀመሪያ ትምህርት አጀማመር የትምህርት ቢሮ ኀላፊዎች በባሕር ዳር ከተማ ተዘዋውረው ተመልክተዋል። የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ ምክትል ቢሮ ኀላፊ እየሩስ መንግሥቱ የመማር ማስተማሩን ሥራ ለማስጀመር የቅድመ ዝግጅት ሥራ ሲሠራ መቆየቱን አስታውቀዋል።

በክልሉ ሰላማዊ በኾኑ አካባቢዎች ላይ የመማር ማስተማሩ ሥራ መጀመሩንም አመላክተዋል። ሰላም በሌለባቸው አካባቢዎች ማስተማር አለመጀሩንም አስታውቀዋል። አብዛኛው የክልሉ አካበቢዎች ትምህርት እንደተጀመረባቸውም ገልጸዋል። የመካከለኛ ደረጃና የመጀመሪያ ደረጃ ተማሪዎች መጽሐፍ እያሰራጩ መኾናቸውን የተናገሩት ምክትል ቢሮ ኀላፊዋ 2 ነጥብ 5 ሚሊዮን መጻሕፍት ማሰራጨታቸውንም አስታውቀዋል። በዓመቱ 7 ነጥብ 4 ሚሊዮን መጻሕፍት እንደሚሠራጩም ተመላክቷል።

በፀጥታ ችግር ምክንያት መጻሕፍትን ማሰራጨት ያልቻሉባቸው አካባቢዎች መኖራቸውንም ተናግረዋል። የፀጥታ ችግር በሌለባቸው አካባቢዎች መጻሕፍትን ከማዕከል እያወጡ እያሰራጩ መኾናቸውንም ገልጸዋል። የመጻሕፍት እጥረትን ለመፍታት እየተሠራ ነውም ብለዋል። ትምህርት በጊዜ ሰሌዳ እንደሚጀመር የተናገሩት ምክትል ቢሮ ኀላፊዋ በጊዜው መጀመር ካልተቻለ በተባለው ጊዜ መጨረስ አይቻልም ነው ያሉት። ዘግይቶ መጀመር በትምህርት ጥራቱ ላይም አሉታዊ ተፅዕኖ እንደሚያሳድር ነው የገለጹት። ለመማርና ለማስተማር ሰላም ወሳኝ ጉዳይ መኾኑንም ተናግረዋል። የሰላም እጦት ሁሉም ተማሪዎች በሰዓቱ እንዳይመዘገቡና ትምህርት እንዳይጀመር እንቅፋት መኾኑንም ገልጸዋል። በክልሉ አንዳንድ አካባቢዎች ላይ ተማሪዎችን በወቅቱ ለመመዝገብ እና የመጀመሪያውን ትምህርት ለማስጀመር እንቅፋት እንደኾነባቸውም ተናግረዋል።

ሁሉም ለሰላም ቅድሚያ በመስጠት የመማር ማስተማሩን ሥራ ምቹ ማድረግ ይጠበቅበታል ነው ያሉት። በዓመቱ 6 ነጥብ 2 ሚሊዮን ተማሪዎችን ለመመዝገብ ማቀዳዳቸውን የተናገሩት ወይዘሮ እየሩስ 2 ነጥብ 7 ሚሊዮን ተማሪዎች መመዝገባቸውንም አስታውቀዋል። ምዝገባ ባልተካሄደባቸው ዞኖች 1 ነጥብ 4 ሚሊዮን ተማሪዎች እንደሚመዘገቡ ይጠበቃል ያሉት ወይዘሮ እየሩስ እስከ መስከረም 25/2016 ዓ.ም በዓመቱ ወደ ትምህርት ቤት መምጣት የሚገባቸው ተማሪዎች እንዲመጡ እየሠራን ነው ብለዋል።

ተማሪዎች በወቅቱ ወደ ትምህርት ቤት እንዲመጡና ክፍለ ጊዜ እንዳይሸራረፍ ለማድረግ እየሠሩ መኾናቸውንም ገልጸዋል። በተገኘው አጋጣሚ ሁሉ የግንዛቤ ፈጣራ ሥራ እየተሠራ ነው ብለዋል። በትምህርት ቁሳቁስ ምክንያት ልጆች ከትምህርት ቤት እንዳይቀሩ እየተሠራ መኾኑን ያነሱት ምክትል ቢሮ ኀላፊዋ ከረጅ ድርጅቶችና ከባለሃብቶች ጋር በመኾን የመማሪያ ቁሳቁስ ለማሟላት እየተሠራ ነው ብለዋል። የፀጥታ ችግሩ ግን እንቅፋት ኾኗል ነው ያሉት።

ዘጋቢ:- ታርቆ ክንዴ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“በሁሉም ትምህርት ቤቶች የመማር ማስተማር ሂደቱ ተጀምሯል” የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን ትምህርት መምሪያ
Next article“በአዲሱ የትምህርት ዘመን የተሻለ ውጤት ለማምጣት ተዘጋጅተናል”ተማሪዎች