
ባሕር ዳር፡- ጥር 17/2012ዓ.ም (አብመድ) በምሥራቅ አፍሪካ የተከሰተውን የአንበጣ መንጋ ለመከላከል የመንግሥታቱ ድርጅት ጥሪ አቀረበ፡፡
በምሥራቅ አፍሪካ ቀጣና አስከፊ የተባለ የአንበጣ መንጋ ተከስቷል፡፡ እንደ ኢትዮጵያ፣ ሶማሊያና ኬንያ ባሉ ሀገራት ታይቶ በማይታወቅ መልኩ ጉዳት እያደረሰ መሆኑንም በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የምግብና የእርሻ ድርጅት (FAO) አስታውቋል፡፡ የበርሃ አንበጣውን በቶሎ መቆጣጣር ካልተቻለ ደግሞ የሀገራቱን ዜጎች ኑሮ ሁኔታ ውስብስብ ሊያደርገው እንደሚችል ተሰግቷል፡፡
እንደ መረጃው የአንበጣ መንጋው ሁሉን እፅዕዋትና አዝዕርት አውዳሚ ከመሆኑ የተነሳ በቀጣናው ሀገራት ኢኮኖሚ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ይፈጥራል፡፡ የመንጋው ብዛትና እያስከተለ ያለው ጉዳት በኢትዮጵና በሶማሊያ በ25ዓመት ውስጥ አስከፊ ሆኖ ተመዝግቧል፤ በኬንያ የታው ደግሞ ከ70 ዓመታት በኋላ የተከሰተ አስከፊው የአንበጣ ወረርሽኝ እንደሆነ ነው የተገለጸው፡፡
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የምግብና የእርሻ ድርጅት እንዳስታወቀው በቅርቡ ወደ ኬንያ የተዛመተው የአንበጣ መንጋ 2 ሺህ 4 መቶ ስኩየር ኪሎ ሜትር መሬት ላይ ነው ያረፈው፡፡ መንጋው እስከ 2 መቶ ቢሊዮን የሚሆን የአንበጣ ስብስብ እንዳለውም ተነግሯል፡፡ በአንበጣ የተሸፈነው የተጠቀሰው መሬትም ከሩሲያዋ ዋና ከተማ ሞስኮ ስፋት ጋር ተቀራራቢነት ያለው ነው፡፡ መቀመጫውን በናይሮቢ ያደረገው የምስራቅ አፍሪካ በርሃ አንበጣ መቆጣጠሪያ ድርጅት እንደገለጸው ደግሞ በኬንያ አንበጣውን ለማጥፋት በሚደረገው ጥረት ዘጠኝ አውሮፕላኖች የኬሚካል ርጭት እያካሄዱና የሚዛመቱባቸው አካባቢዎች ላይም ክትትል እያደረጉ ነው፡፡ ይህም ሆኖ ግን በሚፈለገው ልክ ማጥፋት አልቻለም፡፡
የመንጋው የመራባት አቅም መጨመርና የስርጭት አድማሱ ፈጣን መሆን የምግብ ዋስትና ችግር ውስጥ የሚገኙት እንደ ዩጋንዳና ደቡብ ሱዳን ያሉ የቀጣናው ሀገራት ክፉኛ ሊጎዱ እንደሚችሉ ሥጋት ፈጥሯል፡፡ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ አንበጣውን ለማጥፋት ርብርብ ካላደረገ እስከሚቀጥለው ሰኔ በ5 መቶ እጥፍ ሊጨምር እንደሚችልም ነው የተተነበየው፡፡ በተመድ የምግብና የእርሻ ድርጅት የምስራቅ አፍሪካ ንዑስ አስተባባሪ ዴቪድ ፊሪ እስከ ወርሃ መጋቢት ባሉት ጊዜያት ወረርሽኙ በታየባቸው የምስራቅ አፍሪካ ሀገራት ዝናብ ስለሚዘንብ አንበጣው ለመራባት ምቹ ሁኔታ ሊያገኝ ይችላል የሚል ስጋታቸውን አቅርበዋል፡፡
በሙያዊ ማብራሪያቸውም አንበጣውን ለመከላከል ከአሁኑ የተሻለ ጊዜ ስለማይኖር የሚመለከታቸው ሁሉ ርብርብ ሊያደርጉ ይገባል፡፡ የቀጣናው ሀገራት የተጋረጠባቸውን የአንበጣ ወረርሽኝ አደጋ ለመከላከልም 70 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር እንደሚያስፈልግ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የምግብና የእርሻ ድርጅት ጠይቋል፡፡
ከድርጅቱ ያገኘነው መረጃ እንደሚያመለክተው አንድ የበርሃ አንበጣ ሁለት ግራም የሚሆን ክብደት አለው፡፡ በቀን የክብደቱን ያክል ማንኛውንም አይነት እፅዋዕት መመገብ ይችላል፡፡ 40 ሚሊዮን የሚሆኑ አንበጣዎች አንድ ኪሎ ሜትር ርቀት ያለው ቦታ ሸፍነው በመንጋ የመንቀሳቀስ ሀይል አላቸው፡፡ አንድ በጣም አነስተኛ መንጋ በአንድ ጊዜ በሰብል ላይ ሲያርፍ ደግሞ እስከ 35 ሺህ ሰዎችን በአንድ ቀን ሊመግብ የሚችል እህል ያወድማል፡፡
ምንጭ፡- አልጀዚራ
በኃይሉ ማሞ
