በምክንያት ለመምረጥ የሚያስችለው የፓርቲዎች ክርክር የቱ ነው? በሚዲያ የሚተላለፈው ወይስ በቀጥታ ከሕዝብ ጋር በመገናኘት የሚከናወነው?

234

ፓርቲዎች ክርክር ሲያደርጉ እርስ በእርስ ከመነቋቆር መቆጠብ እንዳለባቸው አስተያዬት ሰጪዎች ተናግረዋል፡፡

የአንድ ሀገር የዴሞክራሲ ባሕል ሊጎለብት የሚችለው ዜጎች በፖለቲካ ተሳትፏቸው ንቁ ሆነው ሲገኙ፣ ገዢውም ሆነ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ሀገሪቱን ሊለውጡ የሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ በመቀራረብ ውይይት ሲያደርጉ ነው፡፡ የኢትዮጵያን የዴሞክራሲያዊ ሂደት የተሻለ ለማድረግ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ለምርጫ እራሳቸውን የሚያስተዋውቁበት መንገድ ሕግን የተከተለ ቢሆን እንደሚመርጡ አብመድ ያነጋገራቸው አስተያየት ሰጭዎች ተናግረዋል፡፡
የባሕር ዳር ነዋሪው አቶ በፍቃዱ መንግስቴ የፖለቲካ ፓርቲዎች ቅስቀሳም ሆነ ክርክር ሲያደርጉ የሀገሪቱ ኢኮኖሚ ላይ ቢመሠረቱና ቢከራከሩ ሀገሪቱ ከፍ ወዳለ ደረጃ መድረስ ትችላለች ብለው ያስባሉ፡፡

በምርጫ ቅስቀሳ ወቅት ብሔርን፣ ማንነትን እና ሃይማኖትን መሠረት ከማድረግ ይልቅ ለኢትዮጵያውያን በሚመጥን መልኩ ከፍ ማለት እንደሚገባም ነው የተናገሩት፡፡ ያደጉትን ሀገራት የምርጫ ቅስቀሳ እንደ ምሣሌ ያነሱት አቶ በፍቃዱ የአሜሪካ የምርጫ ቅስቀሳን ብናይ በሀገሪ ከፍታ ላይ እንጂ በብሔር ሲከራከሩ አይታም ብለዋል፡፡

የፖለቲካ ፓርቲዎች በሚዲያ ቅስቀሳ ከሚያደርጉ ሕዝቡ የሚፈልገውን ጠይቆ ማወቅ እንዲችል ወደ ሕዝቡ ወርደው ውይይት ቢያደርጉ የተሻለ እንደሆነም መክረዋል፡፡ ሕዝቡ በሚፈልገው ጉዳይ ላይ ቢከራከሩ ለሀገሪቱ እድገት እንደሚበጅም ነው ያሰመሩበት፡፡

የደሴ ከተማ ነዋሪው መምህር ይመር ሰኢድ ደግሞ የፖለቲካ ፓርቲዎች እራሳቸውን ለማስተዋወቅ ሚዲያን በመጠቀም ቢሆን ጥሩ ነው ብለው ያምናሉ፡፡ ምክንያታቸው ደግሞ አንድ የፖለቲካ ፓርቲ መድረክ በመፍጠር ከሕዝብ ጋር ቢወያይ ወደ መድረኩ የራሱን አባል ብቻ ሊሰበስብ ይችላል፤ በሚዲያ ከሆነ ግን ሁሉም ማኅበረሰብ የፓርቲውን ማንነት በግልጽ እንዲያውቅ ይረዳል የሚል ነው፡፡ “እርስ በእርስ መሰዳደብ ባይኖር ጥሩ ነው፤ በፊት ይስተዋል የነበረውን የፖለቲካ ፓርቲዎች የመጠላለፍ የምርጫ ቅስቀሳ አገርን ከማፍረስ እና ፓርቲውን ከመበታተን ውጭ ሀገራዊ ፋይዳ አይኖረውም” ብለዋል መምህር ይመር፡፡

የሚደረገው የምርጫ ቅስቀሳ በሚዲያ፣ ከሕዝቡ ጋር በሚደረግ ውይይት ቢካሄድ፤ ነገር ግን ብዙኃኑን ለማግኘት ሲባል ሚዲያን መጠቀሙ የተሻለ እንደሆነ የተናገሩት ደግሞ የአማራ ዴሞክራሲያዊ ኃይል ንቅናቄ (አዴኃን) ሊቀመንበር አቶ ተሥፋሁን አለምነው ናቸው፡፡
‹‹የራስን ርዕዮተ ዓለም ማስተዋወቅ ላይ ትኩረት ቢደረግ መልካም ነው፡፡ ገዢው ፓርቲም ችግሮች ካሉበት ማሳየቱም ተገቢ ነው፡፡ የራሳችንን አማራጭ እና ርዕዮተ ዓለም ስናስተዋውቅ የሌላውን ክፍተትም ሆነ ችግር ሥርዓት ባለው መልኩ እና የሕዝቡን አንድነት በማይሸረሽር መልኩ ማሳየት ይጠበቅብናል፡፡ ውድድር ማለት ደግሞ እኔ የተሻልኩ ነኝ፤ እኔ በተሻለ መልኩ ለሕዝብ አገለግላለሁ ማለት ነው፡፡ ሥርዓት ባለው መልኩ የሌላውን ድክመት ስናሳይ ሕዝቡ ከሌላው የተሻልን መሆናችንን ይረዳል›› ብለዋል፡፡

የምርጫ ቅስቀሳ ለማድረግ ከሁሉ የተሻለ ሊሆን የሚችለው ቀጥታ ከሕዝብ ጋር መወያየት እንደሆነም ሊቀመንበሩ ሀሳብ ሰጥተዋል፡፡ ‹‹በሚድያ የምንቀሰቅስ ከሆነ የምናወራው እኛ ብቻ ነን፤ የሕዝቡን ስሜት መረዳት አንችልም ስለዚህ ከማኅበረሰቡ ጋር መድረክ ፈጥሮ ከሕዝብ የሚነሳውን ጥያቄ በመመለስ የራስን ርዕዮተ ዓለም ማስተዋወቅ አማራጭ የለውም›› ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ናትናኤል ፈለቀ በበኩላቸው በቅስቀሳ ወቅት በቀጥታ ከማኅበረሰቡ ጥያቄ እየተነሳ ውይይት ቢደረግ ጥሩ ነው ብለዋል፡፡ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊው እንዳስረዱት ‹‹ኅብረተሰቡ የሚበጀውን እና የተሻለውን ፓርቲ ለይቶ እንዲመርጥ፣ እራሱ ጥያቄ አንስቶ ተገቢውን ምላሽ እንዲያገኝ ፊት ለፊት መወያየት አስፈላጊ ነው፡፡

ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት እንዲያብብ፤ ጤናማ የሆነ መድበለ ፓርቲ ሥርዓት ያስፈልጋል፡፡ የፖለቲካ ፓርቲዎች ክርክር ሲያደርጉ እርስ በእርስ መነቋቆር ባይኖር ይመረጣል፡፡ ሕዝቡ የሚፈልገው መነቋቆር አይደለም፤ የተሻለ አማራጭ እና ዕውቀት ላይ የተመሠረተ ክርክር ነው፤ የሀገሪቱን ዲሞክራሲያዊ ሂደት ሊያበለጽግ የሚችለውም በዚህ መንገድ ነው›› ብለዋል፡፡

ዘጋቢ፡- ብሩክ ተሾመ

Previous articleጣና በለስ ቁጥር አንድ የሥኳር ፋብሪካ ግንባታን ግንቦት ላይ ለማጠናቀቅ እየተሠራ ነው።
Next articleየአንበጣ መንጋ በምሥራቅ አፍሪካ ሀገራት የርሃብ ሥጋት ፈጥሯል፡፡