
ባሕር ዳር: መስከረም 14/2015 ዓ.ም (አሚኮ)በአማራ ክልል የ2016 ዓ.ም የመጀመሪያው መደበኛ ትምህርት ተጀምሯል።
የመማር ማሰተማር ሥራውን የትምህርት ቢሮ የሥራ ኀላፊዎች እና የባሕርዳር ከተማ አሥተዳደር የሥራ ኀላፊዎች በባሕርዳር ከተማ በሚገኙ ትምህርት ቤቶች እየተመለከቱ ነው።
ተማሪዎችም በዓመቱ የመጀመሪያ የትምህርት መጀመሪያ ቀን ወደ ትምህርት ቤቶቻቸው አቅንተዋል። ለመማር ማስተማር ዝግጁ መኾናቸውንም ተናግረዋል።
የሽምብጥ የመጀመሪያና መለስተኛ ትምህርት ቤት ምክትል ርእሰ መምህር ጋሻው ጥሩነህ የመማር ማስተማር ሥራውን መጀመራቸውን ገልጸዋል። መምህራንም ለማስተማር ዝግጁ ኾነው መምጣታቸውንም ተናግረዋል። መማር ማስተማሩ ከመጀመሩ አስቀድሞ ተማሪዎች ለትምህርት እንዲዘጋጁ ማድረጋቸውንም አመላክተዋል።
ተማሪዎችን እንደ ወትሮው ሁሉ በፈረቃ የመማር ማስተማር ሥራ እንደሚቀጥል ተናግረዋል።
የባሕርዳር ከተማ አሥተዳደር ትምህርት መምሪያ ኀላፊ ኃይለ ማርያም እሸቴ በባሕርዳር ከተማ በሚገኙ ትምህርት ቤቶች የመጀመሪያ ትምህርት መጀመሩን አስታውቀዋል። ትምህርት ቤቶችን ለመማር ማስተማር ሥራ ዝግጁ የማድረግ ሥራ አስቀድሞ መሠራቱንም አመላክተዋል።
በከተማዋ መማር ከሚገባቸው ተማሪዎች መካከል 92 በመቶ የሚኾኑት መመዝገባቸውንም አስታውቀዋል። በቁሳቁስ እጥረት ተማሪዎች ትምህርታቸውን እንዳያቋርጡ እየሠሩ ስለመኾኑም ገልጸዋል።
ዘጋቢ:- ታርቆ ክንዴ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!