“የመውሊድ በዓልን ኢስላማዊ ሥርዓት በጠበቀና አብሮነትን በሚያጠናክር መንገድ ማክበር ይገባል” ሼህ አቡበከር ሱሌይማን (ዶ.ር)

87

ባሕርዳር፡ መስከረም 14/2016 ዓ.ም (አሚኮ) አንድ ሺህ 498ኛውን የነብዩ ሙሐመድ (ሠ.ዐ.ወ) መውሊድ በዓልን ስናከብር ኢስላማዊ ሥርዓትን በጠበቀና አብሮነትን በማጠናከር ሊሆን እንደሚገባ የእስልምና ሃይማኖት መምህሩ ሼህ አቡበከር ሱሌይማን (ዶ.ር)
ሼህ አቡበከር (ዶ.ር) ከኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ጋር በነበራቸው ቆይታ እንደገለጹት፤ በዓሉ የሙስሊሙን ብሎም የሕዝቦችን አንድነት ለማጠናከር፣ ፍቅር እንዲጎለብትና መልካም ሥራዎች እንዲጠናከሩ በማድረግ ጉልህ ሚና አለው፡፡

የመውሊድ በዓል ከነብዩ ሙሐመድ (ሰ.ዐ.ወ) ጋር ያለንን ቅርበት የምናስታውስበትና ታሪካቸውን ለትውልድ የምናስተላልፍበት ነው ሲሉ መምህሩ አስገንዝበዋል።

መሰል በዓላቶችንና መድረኮች በተራ ነገሮች ማሳለፍ አይገባም ያሉት ዶክተር ሼህ አቡበከር፤ ሕዝበ ሙስሊሙ ከዚህ በተለየ መንገድ ለሀገር ጥቅም በሚያስገኝ መልኩ ሊያከብረው ይገባል ብለዋል፡፡

ዶክተር ሼህ አቡበከር እንዳመላከቱት፤ በዓሉን ስናከብር የነብዩ ሙሐመድን (ሠ.ዐ.ወ)መልካም ስብዕና፣ ቸርነት፣ ደግነት፣ ለሰው አሳቢነትና ሩህሩህነት በመላበስና በመተግበር ሊሆን ይገባል።

ከመጥፎ አስተሳሰብ ወደ መልካም መንገድ በመጋበዝ የተሻለ ሀገር እንዲኖረንና የተሻለ ዕድገት ደረጃ ላይ እንድንደርስ አንዳችን ለሌላችን ድጋፍ መሆን ይኖርብናል ሲሉ መልዕክት አስተላልፈዋል።

መውሊድ የነብይ መወለድ ክብረ በዓል ብቻ ሳይሆን ቀድሞ የነበሩት የእስልምና ዕውነታዎች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ ያደረገና ከኢትዮጵያ ጋር ከፍተኛ ቁርኝት ያለው በዓል መሆኑን አንስተዋል።

ኢትዮጵያ የነብዩ መሐመድ ተከታዮች ችግር ባጋጠማቸው ጊዜ መልዕክታቸውን ይዘው ሲመጡ ተቀብላ ያስተናገደች ሀገር በመሆኗ ለውለታዋ በቅዱስ ቁራን ላይ ከ30 በላይ ቃላት ተጽፎ ይገኛል፤ ይህን እንግዳ ተቀባይነትና መረዳዳት ማጠናከር ይገባል ብለዋል፡፡

የነብዩ ሙሐመድ (ሠ.ዐ.ወ) ለተቸገሩ ሰዎች ይረዱና ያዝኑ እንደነበር አውስተው፤ የተቸገሩትን በመርዳት፣ በማገዝ፣ በመተዛዘንና የእርሳቸውን ፈልግ በመከተል በዓሉን በደስታ ማክበር እንደሚገባ ገልጸዋል።

ሕዝበ ሙስሊሙ በዓሉን ሲያከብር ብቻውን ሳይሆን ከተቸገሩት ሰዎች ጋር ጠጋ ብሎ ችግራቸውንና ጭንቀታቸውን በመጋራትና ሸክማቸውን በማቅለል መሆን እንዳለበት ጠቁመው፤ በጎ ማድረጉ የሃይማኖቱ አስተምሮና ግዴታ መሆኑን ማወቅ ይገባል ሲሉ ተናግረዋል።

የነብዩ ሙሐመድ (ሠ.ዐ.ወ) መወለድ ለሰዎች የሐቅ፣ የመልካም ሥነ-ምግባርና ስብዕና፣ የመረዳዳት፣ የፍቅር፣ የእውነተኛ መንገድ ፣ መተዛዘን፣ መደጋገፍ፣ አብሮነትና አንድ የመሆን ምልክት ነው ያሉት ዶክተር ሼህ አቡበከር፣ ቀናነትንና ፍቅርን በማሳየት በዓሉን ማክበር እንደሚገባ ተናግረዋል።

ከጎረቤት ጋር ጥሩ ጸባይንና መልካም ሥነ-ምግባርን በመለዋወጥ፣ ለእስልምናና ሌሎች ሃይማኖቾች ተከታይ ለሆኑ ሰዎች ሁሉ መልካም በመሆን በዓሉ ሊከበር እንደሚገባ ጠቁመዋል።

በዓሉን ስናከብርም አሁን ያለንበትን ሀገራዊ ሁኔታም ሳንዘነጋ ከችግሩ እንድንወጣ ጸሎት ማድረስና የተፈናቀሉትን መጠየቅ ይጠበቅብናል ብለዋል።

ሙስሊሙ ማኅበረሰቡ ከነብዩ ሙሐመድ (ሰ.ዐ.ወ) አስተምሮ ባለመራቅ የእርሳቸውን በጎ ተግባራት አዘውትሮ መተግበርና ለሀገሪቱና ለዓለም ችግሮች የመፍትሔ አካል መሆን ይገባል ሲሉ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article«የዓለም የጸጥታ ዘርፍ ቅኝት የሀገራትን ሉዓላዊነት ያከበረ፣ የባለብዙ ወገን ትብብር እና አካታችነትን የተከተለ ሊሆን ይገባል» አቶ ደመቀ መኮንን ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር
Next articleበ2015 በጀት ዓመት ከ1 ሚሊዮን 200 ሺህ በላይ ዜጎች የሥራ እድል መፍጠሩን የሥራና ሥልጠና ቢሮ ገለጸ።