
አዲስ አበባ: መስከረም 13/2015 ዓ.ም (አሚኮ)ስድስተኛው ”መሥቀል በጉራጌ ”ፌስቲቫል በጉራጌ ዞን ምሁርአክሊል ወረዳ በተክለሃይማኖት ቀበሌ ተካሂዷል። በዚህ ፕሮግራም የኢትዮጵያ ቅርስ ጥበቃ ባለሥልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር ኤልያስ ሽኩር የጉራጌ ባሕላዊ የዳኝነት ሥርዓት (ቂጫ)፣ ቤት አሠራር፣ የጉራጌ ክትፎና ቁሳቁሶች እንዲሁም ጆፎሮ (የጉራጌ መንደር አመሰራረት) በዩኔስኮ እንዲመዘገቡ እንሠራለን ብለዋል።
የጉራጌ ዞን ዋና አሥተዳዳሪ ላጫ ጋሩማ መሥቀል በሁሉም የኢትዮጵያ አካባቢ የሚከበር ታላቅ በዓል ቢኾንም በጉራጌ ሕዝብ ዘንድ ግን ልዩና የማንነቱ መገለጫ ነው ብለዋል። “የመሥቀል በዓል ለጉራጌ ሁሉም ነገሩ ነው” ያሉት ዋና አሥተዳዳሪው የተጣላ የሚታረቅበት፣ የተለያዩ ቤተሰቦች የሚገናኙበት፣ ትዳር የሚመሰረትበት፣ የአብሮነት ችቦ የሚበራበት በዓል እንደኾነ ገልጸዋል።
ጉራጌ ቁጠባን በማስተማር እና ሀገርን በመገንባት ጉልህ አስተዋጽኦ ያበረከተ ስለመኾኑም አንስተዋል። በዓለም ዘንድ የሚያኮሩና ትኩረትን የሚሹ የባሕላዊ፣ ተፈጥሯዊና ታሪካዊ እሴቶች ባለቤት ሕዝብ ነውም ብለዋል። ኢትዮጵያዊያን ይህንን ሊገነዘቡና ለዓለም ሊያስውቁ እንደሚገባም ጥሪ አቅርበዋል። የጉራጌ ዞን ባሕልና ቱሪዝም መመሪያ ኀላፊ ወይዘሮ መሰረት አመርጋ ”በዓሉ የተከበረው በዞኑ ያሉ መልካም እሴቶችን ለማስተዋወቅ በመኾኑ የሚመለከታቸው የፌዴራል ተቋማት ድጋፍ እንዲያደርጉ ጠይቀዋል።
የምሁር አክሊል ወረዳ ዋና ኀላፊ ብስራት ገብሩ መሥቀል በጉራጌ ዘንድ ሲከከበር የኖረ በዓል ነው ብለዋል። ”መሥቀል በጉራጌ” በደማቅ ፌስቲቫልነት መከበር የጀመረው ግን ከዛሬ ስድስት ዓመት በፊት ስለመኾኑ ጠቅሰዋል። በመሥቀል ለሰው ብቻ ሳይኾን ለእንስሳትም ልዩ እንክብካቤ የሚደረግበት ነው። አቶ ብስራት በዓሉ ከመስከረም 12 እስከ 24 የሚከበር እንደኾነ ገልጸው የበዓሉ መከበር የዞኑን መልካም እሴቶች በማስተዋወቅ የቱሪስት መዳረሻ ለማድረግ እና የዞኑን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ነው ብለዋል።
ዘጋቢ:- በለጠ ታረቀኝ ከጉራጌ ዞን
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
