
አዲስ አበባ: መስከረም 12/2015 ዓ.ም (አሚኮ) ሕዝበ ክርስቲያኑ የመስቀል ደመራ በዓልን ሲያከብር ፀሎትና ልመናው በፈጣሪ ፊት ተቀባይነትን እንዲያገኝ በፍፁም ሰላማዊነት ቤተክርስቲያኗ ባዘጋጀችው መርሐ ግብር መሰረት ብቻ እንዲሆን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ጥሪ አቀርባለች።
ቤተክርስቲያኗ የፊታችን ረቡዕ የሚከበረውን የመስቀል ደመራ በዓል ዝግጅት አስመልክቶ በጠቅላይ ቤተክህነት መግለጫ ሰጥታለች። የጠቅላይ ቤተ ክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ እና የባሕር ዳር ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ
ብፁዕ አቡነ አብርሃም በመስቀል አደባባይ የሚከበረውን የደመራ በዓልን አስመልክቶ ባስተላለፉት መልእክት የመስቀል ደመራ በዓል ሲከበር ምዕመኑ ወደ ደመራ ስፍራዎች በማቅናት በዓሉን ሲያከብር ቤተክርስቲያኗ ባዘጋጀችው መርሐ ግብር መሰረት ብቻ መሆን እንደሚገባው ተናግረዋል።
ብፁዕ አቡነ አብርሃም የመግቢያ ባጅ እደላው በሕግና በሥርዓት ትኩረት ተሰጥቶት የሚከናወን መሆኑንም አስገንዝበዋል።
በበዓሉ ላይ የተፈቀደለት አስተባባሪ ብቻ የሚያስተናግድ ሲሆን ያልተፈቀደለት አካል ሲንቀሳቀስ ቢገኝ በወንጀል ያስጠይቃል ብለዋል።
በእለቱ ሰዓትን አክብሮ ሃይማኖታዊ ክዋኔውን በሰለማዊ መንገድ ከማስኬድ ጀምሮ ምዕመኑ ቤተክርስቲያኗ የምትጠቀምበትን እና እውቅና ያለውን ሰንደቅዓላማ ብቻ ይዞ እንዲገኝ አሳስበዋል።
በተጨማሪም ርችት ከመተኮስ መታቀብና ፈቃድ የተሰጣቸው ወጣቶች ብቻ በቦታው የማስተባበር ሚናቸውን እንዲወጡ አሳስበዋል።
እለቱ የክርስትና እና የእስልምና ሃይማኖት በዓላት በጋራ የሚውልበት በመሆኑ ከጥንት ጀምሮ ኢትዮጵያዊያን የሚታወቁበትን አንድነትና ተከባብሮ የመኖር እሴት ለዓለም የሚያሳዩበት ትልቅ ታሪካዊ ቀን ይሆናልም ነው ያሉት።
የመስቀል በዓል የክርስቶስ ፍቅርና ክብር የተገለጠበት ነውና በዓሉን በፍጹም ታዛዥነት ሃይማኖታዊ አስተምህሮው በሚያዘው መንገድ የተዘጋጀውን መርሐግብር ተከትሎ እንዲከበር ቤተክርስቲያኗ ጥሪዋን አቅርባለች።
በበዓሉ ላይ ከ10 ሺህ በላይ ከተለያዩ አብያተ ክርስቲያናት የተውጣጡ ወጣቶች ሃይማኖታዊ ሥርዓቱን ጠብቀው መንፈሳዊ አገልግሎትን በመስጠት እንደሚሳተፉም ታውቋል።
ዘጋቢ:–ቤተልሄም ሰለሞን
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!