በሕገ ወጥ መንገድ ሲዘዋወር የነበረ የጦር መሳሪያ በቁጥጥር ስር ዋለ።

162

ደሴ፡ መስከረም 12/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በሐይቅ መስመር ወደ ደሴ ከተማ የገባ የጦር መሳሪያ በኅብረተሰቡ ጥቆማ በደሴ ከተማ አሥተዳደር ቧንቧ ውኃ ክፍለ ከተማ በግለሰብ ቤት ተገኝቷል።

በባለ ሦስት እግር ተሽከርካሪ(ባጃጅ) ላይ በተሳፋሪ መቀመጫ ውስጥ ክላሽ እና ተተኳሽ ጥይቶች መያዛቸውን በመከላከያ ሠራዊት 46ኛ ክፍለጦር ተወርዋሪ ሻለቃ አዛዥና በደሴ ዙሪያ ኮማንድ ፖስት አባል ሻለቃ ደግሰው ደሻ ተናግረዋል።

በኅብረተሰቡ ጥቆማ በተደረገ ክትትል በቧንቧ ውኃ ክፍለ ከተማ በ11/01/2016 ዓ.ም ከቀኑ 6 ሰዓት አካባቢ በግለሰብ ቤት ሰባት ክላሽ እና 420 ተተኳሽ ጥይቶች መያዛቸውን የገለጹት አዛዡ ለእኩይ ተግባር ለማዋልና ማኅበረሰቡ በሰላም ወጥቶ እዳይገባ ለማድረግ የተሠራ ተግባር እንደኾነም ገልጸዋል።

ለሕገ ወጥ ተግባር የሚያገለግሉ መገናኛ ስልኮች ፣ፓስፖርት እና የቀበሌ መታወቂያዎችም ተገኝተዋል።

በዞኑ የተረጋጋ ሰላም ለመፍጠር ከኅብረተሰቡ ጋር በመናበብ እየተሠራ መኾኑን የገለጹት የ801ኛ ኮር ዘመቻ ኀላፊና በደቡብ ወሎ ዞንና ደሴ ከተማ ኮማንድ ፖስት አባል ሻለቃ መላኩ ጥላው ናቸው። ሕገ ወጥ የጦር መሳሪያ ዝውውር እዳይካሄድ በመፈተሻ ኬላዎች የተጠናከረ ሥራ እየተሠራ ነውም ብለዋል።

ኅብረተሰቡ መሰል እኩይ ተግባራቶችን ሲመለከት ለፀጥታ አካላትና ለኮማንድ ፖስት በመጠቆም አኩሪ ተግባር እየሠራ ነው ያሉት ሻለቃ መላኩ ኅብረተሰቡ ሰላሙን ለማስጠበቅ በቀጣይም ከሠራዊቱ ጎን በመቆም አጋርነቱን ማጠናከር አለበት ብለዋል።

ሕገ ወጥ መሳሪያ አዘዋዋሪ ግለሰቦችን በቁጥጥር ስር አውሎ ተጨማሪ ምርመራዎችን ካደረገ በኃላ ለሕዝቡ ይፋ እንደሚደረግም ከኮማንድ ፖስቱ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

ዘጋቢ:-ሰልሀዲን ሰይድ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleወሎ ዩኒቨርሲቲ ለ15ኛ ጊዜ 2 ሺ 3 መቶ 23 ተማሪዎችን አስመረቀ።
Next article“የመስቀልና የመውሊድ በዓላት ከጥንት ጀምሮ ኢትዮጵያዊያን የሚታወቁበትን አንድነትና ተከባብሮ የመኖር እሴት ለዓለም የሚያሳዩበት ትልቅ ታሪካዊ ቀን ይሆናል” የጠቅላይ ቤተ ክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ እና የባሕር ዳር ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ አብርሃም