
ባሕር ዳር፡- ጥር 16/2012ዓ.ም (አብመድ) የተወሳሰበው የደምቢ ዶሎ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ጉዳይ አሁንም ተጨባጭ መረጃ አልተገኘበትም፡፡
የመታገታቸው ዜና ከተሰማበት ኅዳር 24/2012 ዓ.ም ጀምሮ ተማሪዎቹ ስላሉበት ሁኔታ ግልጽ መረጃ አልተገኘም፡፡ መጀመሪያ አካባቢ አልፎ አልፎ በአጋቾቹ የእጅ ስልኮች ከወላጆቻቸው ጋር ይገናኙ እንደነበር ከእገታ ያመለጠችዋ ተማሪም ሆነ ወላጆች መናገራቸው ይታወሳል፡፡ አሁን ላይ ግን የትና በምን ሁኔታ ውስጥ እንደሚገኙ መረጃ የለም፡፡ የፌዴራል መንግሥቱ ከታገቱት ውስጥ 21 ተማሪዎች ስለመለቀቃቸው መረጃ ቢሰጥም ተማሪዎቹ ከወላጆቻቸው ጋር አልተገናኙም፤ በየትኛውም ቦታ ስለመታዬታቸውም መረጃ አልተገኘም፡፡
ይህ ደግሞ ጥያቄው ጎላ ባሉ መላምቶች እንዲቀጥል አድርጎታል፡፡ መገናኛ ብዙኃኑም፣ ወላጆችም፣ ኅብረተሰቡም ይጠይቃል፤ «ተለቀቁ የተባሉት ተማሪዎች የት አሉ?» በማለት፡፡ መጀመሪያ ላይ ታገቱ የተባሉት 17 በደምቢ ዶሎ ዩኒቨርሲቲ ሲማሩ የነበሩ የአማራ ተወላጅ ተማሪዎች ናቸው፡፡ መንግስት ደግሞ 21 መለቀቃቸውንና ቀሪ ስድስት ተማሪዎችን ደግሞ በከፍተኛ ጥንቃቄ በሚደረግ ክትልል ለማስለቀቅ ጥረት እየተደረገ እንደሆነ መግለጫ ሰጠ፡፡ ከዩኒቨርሲቲው ጋር ተደረገ በተባለ ማጣራት ደግሞ ከ17ቱ መካከል ተማሪዎቼ ናቸው ያላቸው 12ቱን ብቻ ነው፡፡ አሁንም ሌላ አወዛጋቢ መረጃ፡፡
ቁጥራቸው የቱንም ያህል ይሁን ደብዛቸው ከጠፋ 52 ቀናት የሆናቸው ተማሪዎች ያሉበት ሁኔታ በግልጽ አለመታወቁ ግን አሁንም አሳሳቢ ጥያቄ ሆኗል፡፡ አካባቢው የተሰማራው ኮማንድ ፖስት ጉዳዩን እያጣራ እንደሆነ ከመናገር ያለፈ የተለዬ መረጃ መሥጠት አልቻለም፡፡ ከፌዴራል ፖሊስ እና ከሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር የተቋቋመ ቡድን ከሰሞኑ ወደ አካባቢው አምርቶ ጉዳዩን ለማጣራት እንደሞከረ፤ ነገር ግን ተማሪዎቹ ስላሉበት ሁኔታ ተጨባጭ መረጃ ሳያገኝ እንደተመለሰ አብመድ ባደረገው ማጣራት አረጋግጧል፡፡
በቀጣይም ፌዴራል ፖሊስ በመነሻነት ያገኘውንና ሌሎች መረጃዎችን በማካተት ተማሪዎቹ ያሉበትን ሁኔታ ለማረጋገጥ እንደሚሠራ ነው የሚጠበቀው፡፡
ትልቅ ተስፋ ተጣለበት ፍንጭ ይገኛል የተባለው ግን ደምቢ ዶሎ ዩኒቨርሲቲ ትምህርት ሲጀምር ነው፡፡ አሁን ላይ 800 የዩኒቨርሲቲው ተማሪዎች ከዩኒቨርሲቲው ግቢ ውጭ እንደሆኑ ታውቋል፡፡ ትምህርት ሲጀመር ምናልባትም ከታገቱት ተማሪዎች ውስጥ የተለቀቁ ካሉ እና ለመማር ከሄዱ ስለሁኔታው ግልጽ መረጃ ይገኛል ተብሎ ነው የትምህርት መጀመሩ ጉዳይ ትልቅ ተስፋ የተጣለበት፡፡ በአካባቢው የተንቀሳቃሽ ስልክ ኔትወርክ ባለመሥራቱ ትምህርት መቼ እንደሚጀምር መረጃ ለማግኘት አልተቻለም፡፡