
ባሕር ዳር: መስከረም 12/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ወሎ ዩኒቨርሲቲ በመጀመሪያ፣ በሁለተኛና በሦስተኛ ዲግሪ በተለያዩ የሙያ ዘርፎች ሲያሠለጥናቸው የነበሩ 2ሺ 3 መቶ 23 ተማሪዎች አስመርቋል።
በዩኒቨርሲቲው ከተመረቁ ተማሪዎች መካከል ሁለቱ በሦስተኛ ዲግሪ የተመረቁ ናቸው።
ዩኒቨርሲቲው ካስመረቃቸው 2ሺ 3 መቶ 23 ተመሪዎች መካከል 575ቱ ሴቶች ናቸው።
የወሎ ዩኒቨርሲቲ የአካዳሚክ ጉዳዮች ምክትል ፕሬዚዳንት ዶክተር አወል ሰይድ የ2015 ዓ ም የ15ኛው ዙር ተመራቂ ተማሪዎች በሰሜኑ የሀገራችን ክፍል በተከሰተው ጦርነት ዩኒቨርሲቲው የደረሰበትን ውድመት ተቋቁመው በጽናት ለምርቃት የበቁ በመኾናቸው የጽናት ተምሳሌቶች ናቸው ብለዋል።
ተመራቂ ተማሪዎች ያላቸውን ጽናት ተጠቅመው ሥራ ፈጣሪ እንደሚኾኑ ያላቸውን ተስፋ ገልጸዋል።
የእለቱ የክብር እንግዳ አቶ ቴዎድሮስ ፈረደ የ2015 ዓ.ም የመውጫ ፈተና በተሳካ ኹኔታ በማለፍ ለመመረቅ በመብቃታችሁ እንኳን ደስ አላችሁ በማለት ለተመራቂዎች የሥራ መመሪያ አስተላልፈዋል።
በዚህ የምርቃት ሥነሥርዓት ላይ ሁለት በሦስተኛ ዲግሪና አንድ በቀዶ ህክምና ስፔሻሊቲ በጠቅላላው ሦስት ተመራቂዎችን በልዩ ኹኔታ አስመርቋል። እነዚህ ምሩቃን በዩኒቨርሲቲው ታሪክ የመጀመሪያ መኾናቸው ታውቋል።
በምርቃት ሥነሥርዓቱ በዩኒቨርሲቲው ከፍተኛ ውጤት ላስመዘገቡ ተመራቂዎች የሜዳሊያና የዋንጫ ሽልማት ተሰጥቷል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!