
ባሕር ዳር: መስከረም 12/2016 ዓ.ም (አሚኮ)በአማራ ክልል 38 አንደኛና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ተገንብተው ለዘንድሮው የመማር ማስተማር ሥራ ዝግጁ መኾናቸውን የክልሉ ትምህርት ቢሮ አስታውቋል።
ትምህርት ቤቶቹ የተገነቡት በክልሉ የትምህርት ተደራሽነትና ጥራትን ለማረጋገጥ እንዲያግዙ ባለድርሻ አካላትን በማሳተፍ መኾኑን የቢሮው ምክትል ኀላፊ መኳንንት አደመ ገልጸዋል።
በዚህም ተገንብተው ለአገልግሎት ከተዘጋጁት መካከል 13 የሁለተኛ ደረጃና 25 ደግሞ የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች መኾናቸውን አስረድተዋል።
ለትምህርት ቤቶቹ ግንባታም ከ600 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ መደረጉን ያመለከቱት አቶ መኳንንት 33 ሺህ ተማሪዎችን ተቀብሎ ማስተናገድ የሚያስችሉ መኾናቸውን ተናግረዋል።
በ2015 ዓ.ም የተገነቡት እነዚህ ትምህርት ቤቶች ላይ የኅብረተሰቡ ተሳትፎና አስተዋጽኦ እንዳለበትም ጠቁመዋል።
በተለይ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶቹ መገንባት ተማሪዎች በርቀትና አቅም ማነስ ምክንያት ትምህርታቸውን ሳያቋርጡ በአቅራቢያቸው ትምህርታቸውን እንዲከታተሉ ምቹ ኹኔታ መፍጠሩን ገልጸዋል።
በየአካባቢው ያለው ኅብረተሰብም ገንዘብ በማዋጣት ተጨማሪ የመማሪያ ክፍሎችን በመገንባት የመማር ማስተማር ሥራው ውጤታማ እንዲኾን የድርሻውን እየተወጣ እንደሚገኝ አብራርተዋል።
ኢዜአ እንደዘገበው ከደረጃ በታች የሚገኙ ትምህርት ቤቶችን ለማሻሻል በመንግሥት፣በኅብረተሰቡና በሌሎችም ድጋፍ ሰጪዎች እየተደረገ ያለው ጥረት ተጠናከሮ ሊቀጥል እንደሚገባም አቶ መኳንንት አመልክተዋል።
ከዚህም ሌላ ትምህርት ሚኒስቴር በመደበው በጀት 45 የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች እየተገነቡ መኾናቸውን ጠቅሰው፤ እስከ ህዳር ወር 2016 ዓ.ም ተጠናቅቀው ለአገልግሎት እንደሚበቁም ጠቁመዋል።
በዋግህምራ ብሔረሰብ አሥተዳደር ሰቆጣ ዙሪያ ወረዳ የፀመራ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ርእሰ መምህር ግርማ ጌቴ ትምርት ቤቱ በሰሜኑ ጦርነት ከፍተኛ ጉዳት ደርሶበት እንደነበር አስታውሰዋል።
ይህም ደረጃውን ባልጠበቁ ክፍሎች ተማሪዎች እንዲማሩ ማስገደዱን ጠቅሰው፤ አሁን አስር የመማሪያ ክፍሎች በመገንባታቸው ተማሪዎች ትምህርታቸውን በአግባቡ እንዲከታተሉ ያደርጋል ብለዋል።
በትምህርት ቤቱ የአምስተኛ ክፍል ተማሪ አሰፉ አምባዬ በሰጠችው አስተያየት፤ ቀደም ሲል አመቺነት በሌለውና ቆርቆሮ በቆርቆሮ በኾነ ክፍል ሲመሩ መቆየታቸውን ተናግራለች።
አሁን ላይ ደረጃውን የጠበቀ መማሪያ ክፍል በመገንባቱ ተረጋግተው ትምህርታቸውን እንዲማሩ እንደሚያስችላቸው ገልፃለች።
የደሴ ከተማ ነዋሪም ወይዘሮ ራቢዓ የሱፍ ልጆቻቸውን በትግል ፍሬ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ሲያስተምሩ መቆየታቸውን ጠቅሰው፤ ትምህርት ቤቱ በእርጅና ምክንያት በመጎዳቱ ልጆቻቸው ሌላ ትምህርት ቤት አስቀይሩን እያሉ ያስቸገሯቸው እንደነበር አስታውሰዋል።
አሁን ላይ ትምህርት ቤቱ በተሻለ ደረጃ ተገንብቶ ለትምህርት ዘመኑ ምቹ በመኾኑ ልጆቻቸው በደስታ ተመዝግበው ትምህርት የሚጀመርበትን ቀን እየተጠባበቁ ይገኛል ብለዋል፡፡
በአማራ ክልል በዘንድሮ የትምህርት ዘመን ከቅድመ መደበኛ እስከ 12ኛ ክፍል 6 ነጥብ 2 ሚሊዮን ተማሪዎችን ተቀብሎ ለማስተማር ምዝገባ ሲካሄድ መቆየቱን ቀደም ሲል ተገልጿል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!