
ባሕር ዳር: መስከረም 12/2015 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል የተከሰተውን የግሪሳ ወፍ ለመከላከል እየሠራ መሆኑን የክልሉ ግብርና ቢሮ አስታውቋል፡:
የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ የሰብል ልማትና ጥበቃ ዳይሬክተር አግደው ሞላ በምሥራቅ አማራ በኩል ከፍተኛ የሆነ የግሪሳ ወፍ ክስተት መኖሩን ተናግረዋል፡፡
በአንዳንድ የክልሉ አካባቢዎችም ደግሞ የቢጫ ዋግ እየተስፋፋ መሆኑን ነው የገለፁት፡፡
የግሪሳ ወፉን እና የቢጫ ዋግን ለመከላከል ሰፊ ርብርብ እየተደረገ መሆኑንም አመላክተዋል፡፡ በተለይም ሰሜን ሸዋ እና ኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር ላይ ከፍተኛ የሆነ የግሪሳ ወፍ መፈጠሩንም አሳውቀዋል፡፡
የግሪሳ ወፉን ለመከላከል የአውሮፕላን ርጭት ለማድረግ ኬሚካል መጓጓዙንም ገልጸዋል፡፡ በአጭር ጊዜ ውስጥ የኬሚካል ርጭት ለማከናወን ከግብርና ሚኒስቴር ጋር እየተሠራ ነው ብለዋል፡፡
ቢጫ ዋግን ለመከላከል አርሶ አደሮች ሕጋዊ ፈቃድ ካላቸው ነጋዴዎች ኬሚካሉን እየገዙ እንዲጠቀሙም መልእክት አስተላልፈዋል፡፡ ኬሚካሉን የኢትዮጵያ ግብርና ሥራዎች ኮርፖሬሽን በስፋት እንደሚያቀርብ የተናገሩት ዳይሬክተሩ እድሉን በመጠቀም ስርጭቱን መከላከል እንደሚገባም አሳስበዋል፡፡
የግሪሳ ወፍ የተከሰተበት አካባቢ የጸጥታ ችግር ያለበት መኾንና ከሌሎች ክልሎች ጋር የሚዋሰን በመሆኑ ለመከላከል ፈተና ኾኖ መቆየቱንም ገልጸዋል፡፡ ተደራሽ በሆኑ አካባቢዎች ላይ ርጭት እንደሚካሄድ ነው የተናገሩት፡፡ የግሪሳ ወፍን ለመከላከል ከሌሎች ክልሎች ጋር መናበብ እንደሚያስፈልግም ገልጸዋል፡፡
በአንድ ቦታ ላይ በሚሠራ ሥራ ብቻ የግሪሳ ወፍን መከላከል እንደማይቻል ነው ዳይሬክተሩ የተናገሩት፡፡ የግሪሳ ወፍን ከመነሻው ጀምሮ መከላከል ይገባልም ብለዋል፡፡ ከመነሻው ጀምሮ መከላከል ካልተቻለ ጫናው ከባድ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ታርቆ ክንዴ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!