
ባሕር ዳር: መስከረም 12/2016 ዓ.ም (አሚኮ)በአህጉር አቀፍ ውድድሮች ሲሳተፍ በታሪኩ የመጀመሪያ ቢኾንም እያስመዘገበ ያለው ውጤት ግን ተስፋ የሚጣልበት እና ሀገርን የሚያኮራ እንደኾነ ይነገራል፡፡ እንደ አህጉራዊ የእግር ኳስ መሥራችነታቸው ከክለብ እስከ ብሔራዊ ቡድን ውጤት ርቆበት የሚቆዝመው የሀገሪቱ እግር ኳስ አፍቃሪ የእግር ኳስ ትንሣኤዋን እንደ መጻዓት ቀን በተስፋ ይጠባበቃል፡፡ ማን ያውቃል ይኽ ለሀገሪቱ የእግር ኳስ ትንሣኤ አንዱ መንገድ ጠራጊ ቢሆንስ?
ባለፈው ዓመት የኢትዮጵያ ፕሪሜር ሊግ ውድድር በርካታ ስኬቶችን አስመዝግቦ ደጋፊዎቹን ጮቤ ያስረገጠው ባሕር ዳር ከነማ እግር ኳስ ክለብ በአፍሪካ ኮንፌደሬሽን ካፕ ከችግሮቹ የላቀ ውጤት፤ ከተሰጠው ግምት የተጻረረ ድል እያስመዘገበ ይገኛል፡፡ በአፍሪካ የክለቦች ውድድር የላቀ ዝና እና የገዘፈ ሥም ያለውን የታንዛኒያውን እግር ኳስ ክለብ አዛም በደርሶ መልስ ጨዋታ አሸንፎ የመጀመሪያውን ዙር ማጣሪያ ሲያልፍ ብዙዎቹ ይኽ እንደሚኾን መገመት አልቻሉም ነበር፡፡
እንደ አለመታደል ወይም በፈተና ውስጥ በብቃት ማለፈን እንደ ፀጋ ተችሮ በሁለተኛው ዙር የማጣሪያ ውድድር የባሕር ዳር ከነማ ተጋጣሚ የቱኒዚያው ክለብ አፍሪካን ነው፡፡ ክለብ አፍሪካን የእግር ኳስ ክለብ በአፍሪካ የእግር ኳስ ክለቦች ታሪክ ገናና ሥም እና ዝና ከገነቡ ጥቂት ክለቦች ተጠቃሽ ነው፡፡ ከ100 ዓመታት በላይ የኾነ የምሥረታ ታሪክ ያለው ክለብ አፍሪካን ከ60 ሺህ በላይ ተመልካቾችን መያዝ የሚችል ስታዲየም ባለቤት እና የአፍሪካ ቻምፒዮንስ ሊግ የድል ባለቤት ኾኖ ዋንጫውን ያነሳም ታላቅ ክለብ ነው፡፡
በሁለተኛው ዙር የመጀመሪያ ማጣሪያ ጨዋታ በአዲስ አበባ አበበ ቢቂላ ስታዲየም ክለብ አፍሪካን ያስተናገደው ባሕር ዳር ከነማ 2 ለምንም በኾነ ውጤት አሸንፎ ጅማሮውን አሳምሯል፡፡ ከስምንት ቀናት በኋላ በቱኒዚያ የመልስ ጨዋታውን የሚያደርገው ባሕር ዳር ከነማ የ90 ደቂቃ ፍልሚያውን በድል መወጣት ከቻለ ወደ ቀጣይ ዙር ማለፉን ያረጋግጣል፡፡ የመልሱን ጨዋታ በድል ለመወጣት ምን ያክል ዝግጁ ናችሁ ሲል የክለቡን ዋና አሠልጣኝ ደግአረገ ይግዛው አሚኮ በስልክ አነጋግሯል፡፡
አሁን ያለው ክልላዊ የሰላም እጦት በቂ ልምምድ እንዳናደርግ እና በደጋፊዎቻችን መካከል በሜዳችን እንዳንጫዎት አድርጎናል ያሉት አሠልጣኝ ደግአረገ በተጨዋቾቼ ብርቱ ጥረት ውድድሩን በድል ጀምረናል ብለዋል፡፡ በመጀመሪያው ዙር ማጣሪያ 12 የልምምድ መርሐ ግብሮችን በሜዳ እጦት ምክንያት ሰርዘው እና በቂ ያልኾነ ዝግጅት አድርገው ወደ ቀጣዩ ዙር ማጣሪያ አልፈዋል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ አሥተዳደር ስፖርት እና ወጣቶች ቢሮ፣ አራዳ ክፍለ ከተማ ወረዳ 15፣ የቀነኒሳ ሜዳ እና ወጣቶች እና ስፖርት አካዳሚ ኢትዮጵያ ባደረጉላቸው የሜዳ ትብብር ውስን ልምምዶችን ሠርተው እንደነበር ያነሱት አሠልጣኙ የልምምድ ሜዳ እጥረት አሁንም ድረስ ፈተና እንደኾነባቸው ግን ነግረውናል፡፡
በግንባታ ላይ የሚገኘው የአዲስ አበባ ስታዲየም መጠነኛ ልምምድ ማድረግ የሚችሉበት ደረጃ ላይ ስላለ ለቀጣይ ውድድሮች ልምምድ እንዲያደርጉ ፈቃድ ብናገኝ መልካም ነው ብለዋል አሠልጣኙ፡፡
በመጀመሪያው ጨዋታ አዲስ አበባ ላይ 2 ለ 0 አሸንፈናል፤ ቀጣዩን የመልስ ጨዋታም ከስምንት ቀናት በኋላ መስከረም 20/2015 ዓ.ም በቱኒዚያ እናደርጋለን ያሉት አሠልጣኝ ደግአረገ “በአስቸጋሪም ኹኔታም ውስጥ ኾነን ሀገራችን እና ደጋፊዎቻችን የሚያኮራ ውጤት እናስመዘግባለን” ብለዋል፡፡ ተጨዋቾቻቸው ጨዋታውን በድል ለመወጣት የሚያስችል በቂ የሥነ-ልቦና ዝግጅት እንዳደረጉም ነግረውናል፡፡
ዘጋቢ፡- ታዘብ አራጋው
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!