“በአማራ ክልል ከ5 ነጥብ 1 ሚሊዮን ሄክታር በላይ መሬት ታርሷል” ግብርና ቢሮ

35

ባሕር ዳር: መስከረም 12/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ ለ2015/16 የምርት ዘመን ምርትን ለማሳደግ እየሠራ መሆኑን አስታውቋል፡፡ የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ የሰብል ልማትና ጥበቃ ዳይሬክተር አግደው ሞላ በ2015/16 የምርት ዘመን ሰፊ የቅድመ ዝግጅት ሥራዎችን ሠርተው ወደ ሥራ መግባታቸውን አስታውሰዋል፡፡ በምርት ዘመኑ 5 ሚሊዮን ሄክታር መሬት ለማልማት አቅደው ወደ ተግባር መግባታቸውን አስረድተዋል። ዳይሬክተሩ ከሚታረሰው መሬት 160 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ለማግኘት መታቀዱን ገልጸዋል፡፡ ዝናብ የጀመረበት ወቅት ጥሩ በመሆኑ ለልማት ምቹ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡

በክልሉ 5 ነጥብ 1 ሚሊዮን ሄክታር መሬት በላይ መታረሱንም አስታውቀዋል፡፡ በምርት ዘመኑ ከ1 ነጥብ 9 ሚሊዮን ሄክታር በላይ መሬት በኩታ ገጠም ለማልማት ታቅዶ 1 ነጥብ 6 ሚሊዮን ሄክታር መሬት በኩታ ገጠም መሸፈኑንም አመላክተዋል፡፡ በክልሉ በተፈጠረው ወቅታዊ ሁኔታ የሁሉንም ዞኖች መረጃ ማግኘት አለመቻሉ እንጅ አፈጻጸሙ ከዚህ ከፍ የሚልበት እድል እንዳለም ተናግረዋል፡፡

በማዳበሪያ አቅርቦት የአርሶ አደሮችን ፍላጎት ማሳካት እንዳልተቻለ የተናገሩት ዳይሬክተሩ የቀረበውን ማዳበሪያ ለማድረስ ጥረት ማድረጋቸውንም ገልጸዋል፡፡ ዘግይቶ የደረሰውን ማዳበሪያ ለማዳረስ የጸጥታ ችግር ገጥሟቸው እንደነበርም አስታውሰዋል፡፡

የሰብል እንክብካቤው እየተከናወነ መሆኑንም አመላክተዋል፡፡ የፀጥታ ችግሩ እስከታች ወርደው ለመደገፍ እንዳላስቻላቸውም ጠቅሰዋል፡፡

በክልሉ የተወሰኑ አካባቢዎች የዝናብ እጥረት ማጋጠሙን ያነሱት ዳይሬክተሩ እንዳንድ አካባቢዎች ዘር ያልተዘራባቸው፣ አንዳንዶቹ ደግሞ ዘርተው የተቋረጠባቸው መኖራቸውን ነው የገለፁት፡፡ የዝናብ እጥረቱ የፈጠረውን ችግር ለመፍታት የሚያስችል ሥራ በሚቻላቸው ሁሉ እንደሚሠሩም ተናግረዋል፡፡

የዝናብ እጥረት በገጠማቸው አካባቢዎች መንግሥታዊ ካልሆኑ ድርጅቶች ጋር በጋራ በመሆን በቀጣይ ሊደረጉ በሚገባቸው ጉዳዮች ላይ እየሠሩ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡

ዘጋቢ፡- ታርቆ ክንዴ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየሚያጋጥሙ ችግሮችን በመቋቋም ምርትን ለመጨመር እየሠሩ መኾናቸውን የዞን ግብርና መምሪያዎች ገለጹ።
Next article“በአስቸጋሪም ኾኔታም ውስጥ ኾነን ሀገራችን እና ደጋፊዎቻችን የሚያኮራ ውጤት እናስመዘግባለን” አሠልጠኝ ደግአረገ ይግዛው