
ባሕር ዳር: መስከረም 12/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ የ2015/16 የምርት ዘመን ወቅታዊ የግብርና ሥራዎችና የቀጣይ አቅጣጫዎች ላይ ከመሪዎችና ከባለሙያዎች ጋር መክሯል። በምክክሩ ላይ የተገኙ የዞን ባለሙያዎች እና መሪዎች ፈተናዎችን በመቋቋም ምርት እንዲጨምር እየሠሩ መኾናቸውን አስታውቀዋል።
የደቡብ ጎንደር ዞን ግብርና መምሪያ ተወካይ ኀላፊ ቀኝአዝማች መስፍን በዞኑ ለምርት ምቹ የኾነ ቦታ መኖሩን ተናግረዋል። 526 ሺህ ሄክታር የእርሻ መሬት በዞኑ መኖሩን ገልጸዋል። በመኸር ከሚለማው መሬት 17 ሚሊዮን ኩንታል ምርት እንደሚጠበቅም ተናገረዋል።
የታቀደውን ምርት ለማሳካት ሰፋፊ ሥራዎችን መሥራታቸውን የተናገሩት ኀላፊው የግብዓት አቅርቦት ስርጭትና ሌሎች ድጋፎች ሲደረጉ መቆየታቸውን ነው ያስረዱት።
ተከሰቶ የነበረው የማዳበሪያ አቅርቦት ችግር ፈታኝ እንደነበረም ተናግረዋል። አሁን ላይ ያለው የሰላም እጦት ተንቀሳቅሶ ለመደገፍ አስቸጋሪ መኾኑንም ገልጸዋል። በዞኑ ቆላማ አካባቢዎች የዝናብ እጥረት መግጠሙንም አስታውቀዋል። የተከሰቱትን ችግሮች በመቋቋም የግብርና ልማትን ግብ ለማሳካት እየሠሩ መኾናቸውንም አመላክተዋል። በመኸር ወቅት የሚታጣውን ሰብል በቀሪ እርጥበት እና በመስኖ ልማት ለማካካስ እየሠሩ መኾናቸውንም አስታውቀዋል።
በዞኑ በቀሪ እርጥበት 133 ሺህ ሄክታር መሬት ለማልማት ማቀዳቸውንም ተናግረዋል። 46 ሺህ ሄክታር ነባር እና 7 ሺህ ሄክታር አዲስ መሬት በመስኖ ለማልማት መታቀዱንም ገልጸዋል። በመስኖ ከሚለማው መሬት 26 ሺህ ሄክታር የሚኾነው መሬት በስንዴ ሰብል እንደሚሸፈንም አመላክተዋል።
መስኖ በደቡብ ጎንደር ዞን የተለመደ መኾኑን ያነሱት ኀላፊው የማዳበሪያ እጥረት ሊፈትናቸው እንደሚችልም ተናግረዋል። የማዳበሪያ እጥረት ካልገጠመ በስተቀር እቅዳቸውን ለማሳካት የሚያግዳቸው እንደሌለም ነው የተናገሩት።
እየጣለ ያለው ዝናብ ምርትን ለመጨመር እንደሚያስችልም አስረድተዋል። ባለሙያዎቻቸው ሥራ ላይ መኾናቸውንም አስታውቀዋል። ባለፈው ዓመት የገጠመውን የማዳበሪያ እጥረት ችግር ለመፍታት የኮምፖስት ዝግጅት እየተሠራ መኾኑንም ተናግረዋል። 16 ነጥብ 4 ሚሊዮን ሜትር ኪዩብ ኮምፖስት ለማዘጋጀት አቅደው እየሠሩ መኾናቸውን ነው የገለጹት። ወረዳዎች ወደ ኮምፖስት ዝግጅት መግባታቸውንም አመላክተዋል። አሁን ላይ የተፈጠረውን የኑሮ ውድነት ለመዋጋት ግብርና ልማት ላይ ርብርብ ማድረግ እንደሚገባም ተናግረዋል። በየቤቱ የደረሰውን የኢኮኖሚ ችግር ሊፈታ የሚችለው ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ መኾኑንም ገልጸዋል።
የሰሜን ጎጃም ዞን ምክትል አሥተዳዳሪና የግብርና መምሪያ ኀላፊ በቀለ ወርቁ ዞኑ ገና በመዋቀር ላይ ያለ ቢኾንም የግብርና ልማት ላይ እቅዶችን ይዘው እየሠሩ መኾናቸውን ተናግረዋል። እስካሁን የነበሩ ልምዶችን በመጠቀም ለላቀ ምርት እየሠራን ነው ብለዋል። በክልሉ ያለውን ወቅታዊ ሁኔታ በመቋቋም እየሠሩ መኾናቸውንም አስታውቀዋል። ባለፈው የምርት ዘመን ያመለጡንን እድሎች የማካካስና ተጨማሪ ምርትን ለማግኘት የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች ላይ ነንም ብለዋል። የመስኖ ሥራዎችን ለመሥራት የቅድመ ዝግጅት ሥራዎችን እየሠሩ መኾናቸውንም አመላክተዋል። ዞኑ ያለውን የግብርና ምርት አቅም ለመጠቀም እንደሚሠራም ገልጸዋል።
በግብርና ልማት አርሶ አደሮችን ተጠቃሚ ያደረጉ የልማት ሥራዎች መሠራታቸውንም ነው ያስገነዘቡት።
ዘጋቢ:- ታርቆ ክንዴ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!