
ይህ ሰንደቅ እስካሁን ድረስ ከፍ ያላለበት አንድ መድረክ አለ፡፡ ይሄም ከእግር ኳስ ውድድር ሁሉ ትልቁ እንደሆነ በሚታመነው የዓለም ዋንጫ መድረክ ነው፡፡ በዚህ መድረክ ላይ ሰንደቁን ከፍ ለማድረግ ብዙ ጊዜ ጥረት ተደርጓል፤ ነገር ግን አልተሳካም፡፡ ለምን ? ለ2022 የኳታሩ የዓለም ዋንጫ የአፍሪካ ሃገራት የምድብ ድልድል በግብጽ ካይሮ ወጥቷል፡፡ በ10 ምድቦች በተደለደለው የአፍሪካ ሃገራት የዓለም ዋንጫ የምድብ ድልድል ኢትዮጵያ በምድብ ሰባት (በምድብ G) ተደልድላለች፡፡
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በምድብ ሰባት ሲደለደል፣ ደቡብ አፍሪካን፣ ጋናን እና ዝምባቡዌን ይገጥማል፡፡ በተለይም ደቡብ አፍሪካና ጋና በአፍሪካ እግር ኳስ ታሪክ ተጽዕኖ ፈጣሪ የሚባሉ ሃገራት ናቸው፡፡ ደቡብ አፍሪካ በዓለም ዋንጫ ከመሳተፍ ባለፈ የ2010 የዓለም ዋንጫ በማዘጋጀት ታላቅነቷን አስመስክራለች፡፡ ምንም እንኳን በውድድሩ ረጅም ርቀት መሄድ ባትችልም፡፡ ኢትዮጵያ የአፍሪካ እግር ኳስና የአፍሪካ ዋንጫ ጠንሳሽ ብትሆንም ዛሬ ግን የአፍሪካ ዋንጫን ናፋቂ ከሆነች ረጅም ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡ የዓለም ዋንጫ ትኬት በታሪኳ ቆርጣ አታውቅም፡፡ በቀጣይስ ?
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝ አብርሃም መብራቱ ከምድብ ድልድሉ በኋላ በሰጡት አስተያዬት ‹‹የወጣው ድልድል ለአንዳንዱ ቀላል ሲሆን ለሌላው ደግሞ ከባድ ነው፡፡ ብሔራዊ ቡድኑ የተመደበበት ምድብም የሚመጥን ጠንካራ ዝግጅት እንድናደርግ የጠቆመ ድልድል ነው፡፡ ዝግጅታችን በሚገባ አጠናክረን ሁሉም ባለድርሻ አካላት ጥሩ ሥራ ከሠራ ቡድኑ አሁን ያለውን መነሳሳትና ጥንካሬ ማስቀጠል እንችላለን›› ብለዋል፡፡
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ታላላቅ ውድድሮች ላይ መሳተፍ ለምን አቃተው ስንል የዘርፉን ምሁር አነጋግረናል፡፡ በደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ የስፖርት ሳይንስ መምህሩ ዶክተር ኃይለ ኢየሱስ ባዘዘው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ከአፍሪካ ሃገራት ጋር ተጫውቶ ለማሸነፍ የሚቸገረው የሌሎች ሃገራትን የአጨዋወት ስልት የሚመክት አይነት አጨዋወት ስለሌለው ነው ብለዋል፡፡ ኢትዮጵያውያን ተጫዋቾች በቴክኒክ ደረጃ የላቁ እንደሆኑ ቢነገርላቸውም በአካል ብቃት ከሌሎች ሃገራት ጋር ሲነጻጸሩ የደከሙ እንደሆኑም መምህሩ ተናግረዋል፡፡ የሌሎች አፍሪካ ሃገራት በየጨዋታው ይዘውት የሚቀርቡት የአጨዋወት ስልት የተለያዬ መሆኑንም ዶክተር ኃይለ ኢየሱስ አብራርተዋል፡፡
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ግን በእያንዳንዱ ጨዋታ ተመሳሳይ የአጨዋወት ስልት ይዞ መቅረቡ ውጤታማ እንዳላደረገው በአብነት ጠቅሰዋል፡፡ ኢትዮጵያ በቅርቡ ከኮትዲቯር ጋር በነበራት ጨዋታ ዋልያዎቹ በጥሩ መነሳሳት እና ጫና በመፍጠር መጫወታቸውን እንደ መልካም አብነት ጠቅሰዋል፡፡ ያን አይነት የአጨዋወት ስልት የሚደግሙት ከሆነ ብሔራዊ ቡድኑ ወደ ፊት ይሻገራል ብለዋል ዶክተር ኃይለ ኢየሱስ፡፡ ብሔራዊ ቡድኑ የበለጠ ውጤታማ እንዲሆን ተጨዋቾች በእድሜያቸው ልክ በቂ ሥራ መሥራት አለባቸውም ብለዋል፡፡ አሰልጣኞችና ተጫዋቾች በእግር ኳስ ሂደቱ «ጉድለቴ ምኑ ጋ ነው?» የሚለውን ለይተው ማወቅ መቻል እንዳለባቸውም ተናግረዋል፡፡
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ተጫዋቾች የእግር ኳስ ልምምድ ከሚያደርጉት በዘለለ ለአካል ብቃት የሚረዳ የጅም ሥራ እንደማይሠሩ ነው ዶክተሩ የገለጹት ፡፡ «ከልምምድ መልስ አብዛኛውን ጊዜ የሚያሳልፉት በእረፍት ወይም ስፖርታዊ ባልሆነ እንቅስቃሴ ነው» ያሉት ዶክተር ኃይለ ኢየሱስ የአካል ብቃት ክፍተታቸውን ለመሙላት ጅምን በልዩነት መሥራት እንዳለባቸውም መክረዋል፡፡ የአሰልጣኝ አብርሃም ቡድን እድገት እያሳዬ እንደሆነና በዚህ ከቀጠለ ብሔራዊ ቡድኑ ከሚፈለገው ደረጃ እንደሚደርስም ተስፋቸውን ገልጸዋል፡፡
ብሔራዊ ቡድኑ የሚፈርስና በየጊዜው አዳዲስ ብሔራዊ ቡድን እየመሠረቱ የሚሄዱ ከሆነ ግን ውጤታማ መሆን እንደማይቻል ተናግረዋል፡፡ አሁን ያለውን ብሔራዊ ቡድን በማጠናከር ክፍተቱን እየሞሉ መሔድ ከተቻለ ውጤታማ መሆን ይቻላልም ብለዋል፡፡ እንደ ምሁሩ አስተያየት ኢትዮጵያ በምድብ ማጣሪያው የደረሷት ብሔራዊ ቡድኖች ትልልቅ ስም ያላቸው ቢሆኑም ጨዋታውን ለተቃራኒ ብሔራዊ ቡድን ሳይሰጡ መጫወት ከቻሉ ውጤታማ ይሆናሉ፡፡ የኳስ እንቅስቃሴውን ለተቃራኒ ቡድን የሚሰጡ ከሆነ ግን በአካል ብቃት ደካሞች ስለሆኑ በቀላሉ ተጥሰው ግብ ይቆጠርባቸዋል፡፡
ኢትዮጵያ ኮትዲቫር ላይ ባሳየችው ጥንካሬ ቀጥላ በኳታር አደባባይ ላይ ሰንደቋ ከፍ ሲል እናይ ይሆን ? በኳታር አደባባይ ሰንደቋ የሚውለበለብ ከሆነ በሌላኛው ከፍታ ከፍ ብሎ ይታያል፡፡
ዘጋቢ፡-በታርቆ ክንዴ