
ባሕርዳር፡ መስከረም 12/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ሁለተኛው የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የውኃ ሙሌት እና አለቃቀቅ ደንቦች እና መመሪያዎች የሶስትዮሽ ድርድር ዛሬ መስከረም 12 ቀን 2016 ዓ.ም በአዲስ አበባ ተጀምሯል።
የኢትዮጵያ ወገን ተደራዳሪዎች ልኡካን መሪ አምባሳደር ስለሺ በቀለ (ዶ/ር) በመክፈቻ ንግግራቸው ይህ ውይይት እየተካሄደ ያለው እ.ኤ.አ. በ2015 በተደረሰው የመርሆዎች መግለጫ መሰረት በስኬት ከተከናወነው አራተኛው ዙር የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ሙሌት በኋላ መሆኑን ጠቅሰዋል። በመሆኑም በዚህ ዙር ውይይት ሀገራቱ በጉዳዮች ዙሪያ መግባባት ላይ ለመድረስ ያላሰለሰ ጥረት እንደሚያደርጉ ያላቸውን እምነት ገልጸዋል። አያይዘውም በመርሆዎች መግለጫው በተቀመጠው መሰረት በአባይ ውኃ አጠቃቀም ፍትሐዊ እና ምክንያታዊ አጠቃቀም መርህን ማስፈን ብቸኛው አማራጭ መሆኑን ገልጸዋል። በተጨማሪም ሒደቱ በስኬት እንዲጠናቀቅ ኢትዮጵያ እንደ ከዚህ ቀደሙ ሁሉ በቁርጠኝነት የበኩሏን ሚና እንደምትጫወት አረጋግጠዋል።
የግብጽ የውኃ እና መስኖ ሚኒስትር ፕ/ር ሐኒ ሴዊላም እና የሱዳን ተጠባባቂ የውሃ ሚኒስትር ዳውልበይት አብድልረህማን ማንሱር ባሽር በመክፈቻ ንግግሮቻቸው በድርድሩ ሒደት ከስምምነት ላይ ለመድረስ ያላቸውን ፅኑ ተስፋ ገልጸዋል። መረጃው የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ነው።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!