በኢትዮጵያ የታጠበ የድንጋይ ከሰልን በማምረት የውጭ ምንዛሬን ለመቀነስ ከሁለት የሕንድ ኩባንያዎች ጋር ስምምነት ተፈረመ።

51

አዲስ አበባ፡ መስከረም 12/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ኢትዮጵያ በዓመት 2 ነጥብ 21 ሚሊዮን ቶን የታጠበ የድንጋይ ከሰል ምርት ትፈልጋለች።

ይህን ፍላጎት ለማሳካትም ከተለያዩ ሀገራት ወደ ሀገር ውስጥ ለማስገባትም በአማካይ 227 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር ወጭ ታወጣለች።

ይህን ወጭ ለማስቀረትም የድንጋይ ከሰል ማጠቢያ ፋብሪካ ገንብታለች።

የታጠበ የድንጋይ ከሰል አምርቶ ለመጀመሪያ ጊዜ ለፋብሪካዎች ግብዓትነት ማቅረብ የጀመረው ደግሞ ዮ ሆልዲንግ ንግድ እና ማኑፋክቸሪንግ ኀላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር ነው።

ማኅበሩ የማቀነባበር እና የከሰል ማምረት ሂደቱን የረጅም ጊዜ ልምድ ካላቸው ሁለት የሕንድ ኩባንያዎች ጋር በጋራ ለመሥራት ስምምነት መፈጸሙን በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ገልጿል።

በቤንሻንጉል ጉምዝ ክልል ሥራ የጀመረው ይህ ፋብሪካ በሰዓት 150 ቶን እንዲሁም በዓመት 1 ሚሊዮን ቶን የታጠበ የድንጋይ ከሰል ምርት ሀገር ውስጥ ለሚገኙ የሲሚንቶ፣ የብረት፣ የወረቀት፣ የሴራሚክ፣ የጂፕሰም እና ለሌሎች ፋብሪካዎች በግብዓትነት የማቅረብ አቅም እንዳለው የገለጹት የ ዮ ሆልዲንግ ንግድ እና ማኑፋክቸሪንግ ኀላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር ምክትል ሥራ አስፈፃሚ አታክልቲ ተስፋዬ ናቸው።

ፋብሪካው በመቶዎች ለሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን ቀጥተኛ የኾነ የሥራ ዕድል ከመፍጠሩም በላይ በአካባቢው ለሚኖሩ በርካታ ዜጎች ኢኮኖሚያዊ እና ማኅበራዊ ጠቀሜታ እንዳለው አቶ አታክልቲ አስረድተዋል።

ፋብሪካው በሙሉ አቅሙ አገልግሎት መስጠት ሲጀምር ሀገሪቱ በዘርፉ ያላትን ዓመታዊ ፍላጎት ከማሟላት አንፃር ከፍተኛውን ድርሻ በመወጣት የምታወጣውን ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ ጫና እንደሚያቃልል አብራርተዋል።

ፋብሪካው በአጭር ጊዜ ውስጥ ምርቱን ለሚፈልጉ ሀገራት በመላክ ተጨማሪ ምንዛሬ እንደሚያስገኝላትም ተጠቅሷል።

ዘጋቢ፦ ቤቴል መኮንን

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleኢትዮጵያ እና የተባበሩት አረብ ኢሚሬቶች ትብብራቸውን ለማሳደግ ተስማሙ።
Next articleየታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብን በተመለከተ የኢትዮጵያ፣ ግብጽ እና ሱዳን የሦስትዮሽ ሁለተኛ ዙር ውይይት ተጀመረ።