
👉 250 ሺህ ሄክታር በላይ ማሳ በስንዴ በመሸፈን 10 ሚሊዮን ኩንታል ለማግኘት ታቅዷል
ባሕርዳር፡ መስከረም 12/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ የ2015/16 ዓ.ም የምርት ዘመን ወቅታዊ የግብራና ሥራዎችና የቀጣይ አቅጣጫዎች ላይ ከመሪዎችና ከባለሙያዎች ጋር እየመከረ ነው።
በምክክሩ ላይ መልእክት ያስተላለፉት የግብርና ቢሮው ምክትል ቢሮ ኀላፊ አጀበ ስንሻው የቅድመ ዝግጅት ሥራዎችን በመሥራት በቀጣይ በሚኖሩ ሥራዎች ላይ መረባረብ ይገባል ብለዋል።
በአማራ ክልል 333 ሺህ ሄክታር መሬት በመስኖ በማልማት ከ40 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ለማግኘት እየተሠራ ነው ተብሏል። የመስኖ ልማትን ማሳካት ግድ እንደሚልም አንስተዋል። በክልሉ ሊታጣ የሚችለውን የምርት ጭማሪ ማካካስ የሚቻለው በመስኖ ልማት መኾኑንም ገልጸዋል።
በግብዓት እጥረትና በግጭት ሊታጣ የሚችለውን ምርት ለማካካስ በመስኖ ልማት ላይ ትኩረት ይደረጋል ነው ያሉት። የአማራ ክልል ለመስኖ ልማት የተመቸ መኾኑን ያነሱት አቶ አጀበ ሰፊ መሬት እና የመስኖ አማራጭ ያለው መኾኑንም ገልጸዋል። የስንዴ ምርት ልዩ ትኩረት እንደሚሰጠውም አመላክተዋል። 250 ሺህ ሄክታር በላይ ማሳ በስንዴ በመሸፈን 10 ሚሊዮን ኩንታል ለማግኘት ግብ እንደተቀመጠም ተናግረዋል። በክልሉ በሰላም እጦቱ ምክንያት የግብዓት አቅርቦትን እንደፈለጉ ለማንቀሳቀስ አዳጋች እንደኾነ ያነሱት ምክትል ቢሮ ኀላፊው ችግሮችን ተቋቁመን ግብን ማሳካት ግድ ይላል ብለዋል። በአካባቢው ሰላምና መረጋጋትን ለማምጣት ምርት ማምረት ግድ እንደሚልም አመላክተዋል።
ሁሉንም የመስኖ አቅም አሟጦ ወደ ሠራ መግባት ግዴታችን ነውም ብለዋል። የተፈጥሮ ልማት ሥራዎች በቀጣይ ትኩረት የሚሰጥባቸው ጉዳዮች መኾናቸውንም አንስተዋል። በክልሉ 376 ሺህ ሄክታር መሬት በላይ የአፈርና ውኃ እቀባ ሥራ እንደሚሠራም ገልጸዋል። የአፈርና ውኃ እቀባ ሥራው ስኬታማ እንዲኾን ቅድመ ዝግጅት ማድረግ ይገባል ነው ያሉት። ግብርና ከደከመ የክልሉ አጠቃላይ ኢኮኖሚ ይዳከማል ያሉት አቶ አጀበ ግብርናውን በልዩ ትኩረት መሠራት ይገባል ብለዋል።
በግብርናው ዘርፍ ለወጣቶች የሥራ እድል መፍጠርና ኢንዱስትሪዎችን መደገፍ በትኩረት የሚሠራባቸው ጉዳዮች መኾናቸውንም አንስተዋል። አሁን ላይ ያለው ችግር የሚፈታው በግብርና በሚፈጠረው እድገት ላይ መኾኑንም ተናግረዋል።የግብርና መሪዎች እና ባለሙያዎች እቅዶች እንዲሳኩ በመግባባት፣ በቁርጠኝነት እና በአንድነት እንዲሠሩም አሳስበዋል።
ዘጋቢ:- ታርቆ ክንዴ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!