የደብረ ብርሃን ከተማ መሠረት ልማት መምሪያ በተያዘው በጀት ዓመት በ721 ሚሊየን ብር የተለያዩ መሠረተ ልማቶች እንደሚሠሩ አስታወቀ።

64

ባሕርዳር፡ መስከረም 12/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የደብረ ብርሃን ከተማ መሠረት ልማት መምሪያ የ2016ዓ.ም የካፒታል ኢንቨስትመንት ዕቅድ ለባለድርሻ እና አጋር አካላት አስተዋውቋል።

በዕቅድ ትውውቁ የደብረ ብርሃን ከተማ ብልጽግና ፓርቲ የፖለቲካ ዘርፍ ኃላፊ አቶ ታጠቅ ገድለአማኑኤልን ጨምሮ የከተማ፣ የክፍለ ከተማ፣ የቀበሌ አመራሮችና ከየቀበሌው የተመረጡ የሕዝብ ተወካዮች ተሳትፈዋል፡፡

የከተማው መሠረት ልማት መምሪያ ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ነብዩ ባዩ እንደገለጹት በ2016ዓ.ም በከተማው በሚገኙ በ5ቱም ክፍለ ከተሞች መንገድ፣ መብራት፣ ውሃ፣ ተፋሰስ፣ ድልድይ፣ ሼድና ሌሎች መሠረተ ልማቶችን ለማከናወን በአጠቃላይ 721 ሚሊየን ብር በጀት መያዙን አስታውቀዋል፡፡ የሀብት ምንጩ የዓለም ባንክ፣ የክልሉ መንግስትና የከተማው አሥተዳደር መሆናቸውንም ጠቁመዋል፡፡

ከአዲስ መሠረተ ልማቶች ግንባታ ጎን ለጎን ተንከባላይ ፕሮጀክቶችን የማጠናቀቅ፤ የተጎዱ የኮብልና የጠጠር መንገዶችን የመጠገን ተግባራት እንደሚከናወኑ አመልክተዋል፡፡

በተጨማሪም ጠጠር መንገዶችን ወደኮብል፣ኮብል መንገዶችን ደግሞ ወደ አስፓልት ለመቀየር እንደሚሰራም ተናግረዋል፡፡

ፕሮጀክቶቹ በዕቅዳቸው መሠረት እንዲፈጸሙ በየደረጃው የሚመለከታቸው አካላትና ህብረተሰቡ ተባብረው መስራት እንዳለባቸው አስገንዝበዋል፡፡

የከተማ አሥተዳደሩ ኮሙኒኬሽን መረጃ እንደሚያሳየው በ2015 ዓ.ም ለተለያዩ መሠረተ ልማቶች ከ287 ሚሊየን ብር በላይ ሥራ ላይ መዋሉ ተጠቁሟል፡፡

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleዩኒሴፍ እና ኦቻ የኢትዮጵያን የሰላም ግንባታ ሂደት መደገፋቸውን እንደሚቀጥሉ ገለጹ።
Next article“ሁሉም የመስቀል ደመራ በዓል የሰላም አምባሳደር ሊሆን ይገባል” የአዲስ አበባ ከተማ ሃይማኖት ተቋማት ጉባዔ