
ባሕርዳር፡ መስከረም 12/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የተባበሩት መንግስታት የሕጻናት መርጃ ድርጅት (ዩኒሴፍ) እና የተባበሩት መንግስታት የሰብዓዊ ጉዳዮች ማስተባባሪያ ጽህፈት ቤት (ኦቻ) የኢትዮጵያን የሰላም ግንባታ ሂደት ቀጣይነት ባለው መልኩ ለመደገፍ ፍላጎት እንዳላቸው አስታወቁ።
በኒው ዮርክ እየተደረገ ካለው 78ተኛው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባኤ በተጓዳኝ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ከዩኒሴፍ ዋና ዳይሬክተር ካትሪን ሩሴልና ከኦቻ ኃላፊ ማርቲን ግሪፊትስ ጋር ተወያይተዋል።
አቶ ደመቀ ለሩሴልና ግሪፊትስ በኢትዮጵያ ስላለው ወቅታዊ ሁኔታ ገለጻ አድርገውላቸዋል።
ኢትዮጵያ የፕሪቶሪያ የሰላም ስምምነትን ለመተግበር፤ የመልሶ ማገገምና መልሶ ግንባታ ስራዎችን ለማፋጠን ቁርጠኛ አቋም እንዳላት ገልጸዋል።
ዩኔሴፍ በኢትዮጵያ ለሕጻናት በትምህርትና ጤና ዘርፎች እያደረገ ያለውንም ድጋፍ አድንቀዋል።
በውይይቱ የኦቻ ኃላፊ በኢትዮጵያ የተቋረጠውን የሰብዓዊ እርዳታ ማስቀጠል ያለውን ፋይዳ ለአቶ ደመቀ አንስተውላቸዋል።
የዩኒሴፍና ኦቻ ኃላፊዎች ሁለቱ ተቋማት ለሰላም ግንባታ ሂደቱ ከኢትዮጵያ ጋር የጀመሩትን ትብብር የመቀጠል ፍላጎት እንዳላቸው መግለጻቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታውቋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!