ከተማሪዎች ምዝገባ በተጓዳኝ 750 ሺህ የአዲሱ ሥርዓተ ትምህርት መጽሐፍት መሰራጨቱን የደቡብ ወሎ ዞን ትምህርት መምሪያ ገለጸ።

57

ባሕር ዳር: መስከረም 11/2016 ዓ.ም (አሚኮ)ከተማሪዎች ምዝገባ በተጓዳኝ በ14 ወረዳዎች ለሚገኙ የ1ኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች 750 ሺህ የአዲሱ ሥርዓተ ትምህርት መጽሐፍት መሰራጨቱን የደቡብ ወሎ ዞን ትምህርት መምሪያ ገልጿል።

በመምሪያው የትምህርት ስታቲስቲክስ ሥልጠና እቅድ ዝግጅት እና ሃብት ማፈላለግ ቡድን መሪ አሕመድ አደፋ እንዳሉት በዞኑ እስከ መስከረም 9/2016 ዓ.ም ድረስ ከ490 ሺህ 730 በላይ ተማሪዎች ተመዝግበዋል። ይህም የእቅዱን 64 በመቶ ማሳካት ተችሏል ብለዋል።

👉 ቅድመ አንደኛ ለመመዝገብ ከታቀደው 109 ሺህ 258 ተማሪዎች ውስጥ 76 በመቶ ተመዝግበዋል።

👉 ንጥር ቅበላ ለመመዝገብ ከታቀደው 92 ሺህ 851 ተማሪዎች ውስጥ 50 በመቶ መመዝገብ ተችሏል።

👉 ከ1 እስከ 8ኛ ክፍል ለመመዝገብ ከታቀደው 439 ሺህ 114 ተማሪዎች ውስጥ 74 በመቶ ተመዝግበዋል።

👉 የ2ኛ ደረጃ ተማሪዎችን ለመመዝገብ ከታቀደው 125 ሺህ 700 ተማሪዎች ውስጥ 31 በመቶ ገደማ መመዝገብ መቻሉን ገልጸዋል።

የ8ኛ ክፍል ውጤት አለመገለጽ እና የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ቁጥር ውስን መኾናቸውን ተከትሎ ርቀት ቦታ ተጉዘው የሚማሩ ተማሪዎች በመኖራቸው የትምህርት አጀማመርን መሠረት አድርጎ ምዝገባ ለማከናወን ካለ ፍላጎት ምክንያት የ2ኛ ደረጃ ተማሪዎች ምዝገባ መቀነስ አሳይቷል ብለዋል ቡድን መሪው።

በክልሉ አንዳንድ አካባቢዎች በተከሰተው ወቅታዊ የጸጥታ ችግር ምክንያት በመርሐ ግብሩ መሠረት ምዝገባውን ማከናወን አለመቻሉ ለመቀነሱ ሌላኛው ምክንያት እንደኾነ ተነስቷል።

ከመስከረም 14/2016 ዓ.ም የትምህርት ማስጀመር በተጓዳኝ የትምህርት ምዝገባውን በማስቀጠል በአጭር ጊዜ ለማጠናቀቅ እየተሠራ እንደሚገኝም ነው ቡድን መሪው የገለጹት። ለዚህ ደግሞ የዞኑ የሥራ ኀላፊዎች፣ ወጣቶች፣ የትምህርት ባለሙያዎች እና መምህራንን በማሳተፍ የምዝገባ ሥራው እየተከናወነ ይገኛል ብለዋል።

ከትምህርት ምዝገባ በተጓዳኝ በ14 ወረዳዎች ለሚገኙ የ1ኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች 750 ሺህ የአዲሱ ሥርዓተ ትምህርት መጽሐፍት ተሠራጭቷል። የስድስት ወረዳዎች ደግሞ በመጓጓዝ ላይ ይገኛል ነው ያሉት። በቅርብ ጊዜም ተደራሽ ይኾናል ብለዋል።

በዞኑ 1 ሺህ 207 የ1ኛ ደረጃ እና 67 የ2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ይገኛሉ።

ዘጋቢ፦ ዳግማዊ ተሠራ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“ማኅበራዊ ሚዲያዎች ስለ ኮረና ቫይረስ ክትባቶች የጎንዮሽ ጉዳት ያወጡት መረጃ የተሳሳተ ነው” የበሽታ መቆጣጠሪያ እና መከላከያ ማዕከል(CDC)
Next articleዩኒሴፍ እና ኦቻ የኢትዮጵያን የሰላም ግንባታ ሂደት መደገፋቸውን እንደሚቀጥሉ ገለጹ።