“ኢትዮጵያ በ78ኛው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባዔ ስኬታማ የዲፕሎማሲ ሥራ እያከናወነች ነው” አምባሳደር ተስፋዬ ይልማ

37

ባሕር ዳር: መስከረም 11/2016 ዓ.ም (አሚኮ)ኢትዮጵያ በአሜሪካ ኒውዮርክ እየተካሄደ ባለው 78ኛው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባዔ ስኬታማ የዲፕሎማሲ ሥራ እየሠራች መኾኑን በተ.መ.ድ የኢትዮጵያ ቋሚ መልዕክተኛ አምባሳደር ተስፋዬ ይልማ ገልጸዋል።

78ኛው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባዔ “ሰላም፣ ብልጽግና፣ ለውጥና ዘላቂነት” በሚል መሪ ሀሳብ በመከናወን ላይ ይገኛል።

በተ.መ.ድ የኢትዮጵያ ቋሚ መልዕክተኛ አምባሳደር ተስፋዬ ይልማ ኢትዮጵያ በጉባዔው ያላትን ተሳትፎ አስመልክቶ ማብራሪያ ሰጥተዋል።

በማብራሪያቸውም ኢትዮጵያ ከዋናው ጉባዔው ጎን ለጎን ከተለያዩ ሀገራት ጋር የሁለትዮሽ ውይይት ማድረግ መቻሏን ጠቁመዋል።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ከተለያዩ ሀገራት ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች ጋር መምከራቸውን ጠቁመዋል።

ከዓለም አቀፍ ተቋማትና አጋር አካላት ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ጋር በሁለትዮሽ፣ በቀጣናዊና በባለብዙ ወገን የትብብር ጉዳዮች ውይይት ማድረጋቸውንም እንዲሁ።

በዚህም ሀገራቱ ኢትዮጵያ የጀመረችው የለውጥ ጉዞና የሰላም ሂደት በትክክለኛ አቅጣጫ እየሄደ መኾኑን የጋራ መግባባት ተፈጥሮበታል ነው ያሉት።

በሌላ በኩል ኢትዮጵያ በተለያዩ ሀገራትና ተቋማት በተዘጋጁ የጎንዮሽ የውይይት መድረኮች ተሳትፎ በማድረግ ያላትን አቋም ማስረዳቷንም ገልጸዋል።

በዚህም የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ማሻሻያ እንደሚያስፈልግና አፍሪካ በጸጥታው ምክር ቤት ቋሚ መቀመጫ እንዲኖራት ድምጿን ማሰማቷን ተናግረዋል።

በተለይም ደግሞ በጠቅላላ ጉባዔው ኢትዮጵያ ያላትን እውነታ በሚገባ ማስረዳትና አቋሟንም በትክክል ማንፀባረቅ መቻሉን አመልክተዋል።

ከዓለም አቀፍ ተቋማትና የተለያዩ ኩባንያዎች ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ጋር የተደረጉ ውይይቶች ፍሬያማ መኾናቸውን አስረድተዋል።

ዓለም አቀፍ ተቋማት የፋይናንስ ድጋፍ ለማድረግና ኩባንያዎች በኢትዮጵያ መዋዕለ-ንዋያቸውን ለማፍሰስ ያሳዩት ፍላጎት ተስፋ ሰጪ መሆኑን ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ በአገር አቀፍ፣ ቀጣናዊና ዓለም አቀፋዊ ጉዳዮች ያላትን ምልከታና አቋም የምታንፀባርቅበት የፖሊሲ ንግግር በጠቅላላ ጉባዔው ላይ እንደምታደርግ ጠቁመዋል።

በአሜሪካ ኒውዮርክ እየተካሄደ ያለው 78ኛው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባዔ እስከ መስከረም 15 ቀን 2016 ዓ.ም የሚቆይ ይሆናል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“የሀገር ሽማግሌዎች፣ የሃይማኖት አባቶችና ወጣቶች ለሰላም ዘብ ሊቆሙ ይገባቸዋል።” ሜጀር ጀኔራል ሙሉዓለም አድማሱ
Next article“ማኅበራዊ ሚዲያዎች ስለ ኮረና ቫይረስ ክትባቶች የጎንዮሽ ጉዳት ያወጡት መረጃ የተሳሳተ ነው” የበሽታ መቆጣጠሪያ እና መከላከያ ማዕከል(CDC)