አርሶ አደሮች እና ከተሜው ስለ ምርጫው ተስፋም ሥጋታቸውን ተናገሩ፡፡

109

ባሕር ዳር፡- ጥር 15/2012ዓ.ም (አብመድ) ከሀገራዊ ምርጫው አስቀድሞ መሥተካከል ላለባቸው መሠረታዊ ጉዳዮች መንግሥት ትኩረት እንዲሰጥ አስተያዬት ሰጪዎች ጠየቁ፡፡

የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ በወርሃ ነሃሴ ጠቅላላ ምርጫ ለማካሄድ ዝግጅት እያደረገ መሆኑን በጊዜያዊ መርሃ ግብሩ ማሳወቁ ይታወሳል፡፡ ምርጫው ይዟቸው ሊመጣ የሚችሉ መልካም እድሎች እና ሊኖሩ በሚችሉ ተያያዥ ችግሮች ዙሪያ አብመድ የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎችን አነጋግሯል፡፡ በባሕር ዳር ዙሪያ ወረዳ ደቅ ደሴት ነዋሪው አርሶ አደር ሀይማኖት አረጋ ስለ ሃገራዊ ምርጫው ሁለት አይነት ሀሳብ አላቸው፡፡ ካለፉት ምርጫዎች ልምዳቸው በመነሳትም አዎንታዊ ጎኑ ሊያመዝን እንደሚችል ተናግረዋል፡፡

የሕዝብ እሮሮና የመልማት ብሶት በምርጫ ወቅት ትኩረት ሲያገኙ መመልከታቸውን ነው በማሳያነት ያቀረቡት፡፡ እርሳቸው በሚኖሩበት አካባቢ ባለፈው የምርጫ ዘመን የተተከሉ የኤሌክትሪክ ምሰሶዎች አገልግሎት ሳይሰጡ መቆማቸውን ጠቅሰው የአካባቢው ሰዎች በቅርቡ ይካሄዳል ተብሎ በሚጠበቀው ምርጫ “ኤሌክትሪክ ሃይል ይዘረጋልናል” ብለው እንደሚጠብቁ ነው አርሶ አደሩ የተናገሩት፡፡ ምርጫው ቢካሄድ ሕዝብ የሚያነሳቸው ጥያቄዎች መልስ ሊያገኙ እንደሚችሉም እምነታቸውን ተናግረዋል፡፡

በሌላ በኩል ደግሞ የሰዎች ዕለታዊ እንቅስቃሴ አደጋ ውስጥ ስለወደቀና መንግሥት የህግ የበላይነትን ለማስከበር ስለተሳነው ምርጫ የችግሩ መውጫ ነው የሚል ሀሳብ አላቸው፤ አርሶ አደር ሀይማኖት፡፡ በመሆኑም ምርጫው በተያዘለት ጊዜ ቢካሄድ በሕዝብ ይሁንታን አግኝቶ የሚዋቀረው መንግስት የሕዝቡን ደኅንነት፣ ማኅበራዊና ኢኮኖሚ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የሚያስችል አቅም እንደንደሚያገኝ ተናግረዋል፡፡ በየጊዜው የሚታየውን ማፈናቀል፣ ግድያ፣ አፈና እና ሌሎች ለሀገሪቱ እንግዳ ድርጊቶችን ነው አርሶ አደሩ ለሥርዓት መጥፋቱ በማሳያነት ያነሷቸው፡፡

በአዲስ አበባ ከተማ በንግድ ሥራ ላይ የተሰማሩት አቶ መርሻ መንገሻና በምስራቅ ጎጃም ዞን ደብረ ወርቅ ከተማ ነዋሪው አቶ ብዙ ዓለም ካሳሁን ደግሞ ምርጫው ከመካሄዱ በፊት የሃገሪቱ ነባራዊ ሁኔታ ሊጤን እንደሚገባ ነው የተናገሩት፡፡ አስተያዬት ሰጪዎቹ በሃገሪቱ ያለው አለመረጋጋት ከምርጫው በላይ እንደሚያሳስባቸው ተናግረዋል፡፡ የሕዝብ ደኅንነት ቅድሚያ እየተሰጠው ባለመሆኑ መንግሥትና የሚመለከታቸው አካላት ከምርጫ በፊት ሃገር በማዳን ተግባር ላይ ሊጠመዱ እንደሚገባም ነው የሚያምኑት፡፡

በተወሰኑ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሚታየው የሠላም እጦት፣ ብሔር እና ሃይማኖት ተኮር ግጭቶች በዜጎች ሁለንተናዊ እንቅስቃሴ ላይ ስጋት መሆናቸውን አስተያዬት ሰጪዎቹ በማሳያነት አንስተዋል፡፡ በመሆኑም እነዚህንና መሰል ችግሮችን ይዞ ወደ ምርጫ ቢገባ ለሃገሪቱ ተጨማሪ የብጥብጥ ምክንያት መፍጠር እንዳይሆን ስጋታቸውን ተናግረዋል፡፡
እናም ሕዝቡን ወክለናል የሚሉ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ ለሠላምና ለፍትህ ቆመናል የሚሉ የማኅበረሰብ አንቂዎች ‹‹እኛ እናውቅልሃለን›› ከሚል ግትር አቋም መውጣት እንዳለባቸው ነው የመከሩት፡፡ ለችግሩ መፍትሄ የማፈላለግ ሥራዎች ላይ ትኩረታቸውን ሊያደርጉ እንደሚገባም ሀሳብ ሰጥተዋል፡፡

አብዛኛዎቹ የፖለቲካ ፓርቲዎች አሰላለፋቸው እንጅ ያነገቡት የለውጥ ፖሊሲ ግልጽ አለመሆኑን የተናገሩት አስተያዬት ሰጪዎቹ የምርጫ ጊዜው እየተቃረበ በመሆኑ የተደራጀና ሕዝብን ሊጠቅም የሚችል የፖሊሲ አማራጭ ይዘው ለመምጣት የቅድመ ዝግጅት ማነስ ሊገጥም እንደሚችልም ስጋታቸውን ገልጸዋል፡፡

ከዚህ ጋር ተያይዞ ምርጫው የሚካሄደው በክረምት ወር በመሆኑ መራጩ በሚፈለገው ልክ ሊሳተፍ እንደሚያዳግት ነው ስጋታቸውን ያስቀመጡት፡፡ አርሶ አደሮች በክረምት ደራሽ ሥራዎች ሊጠመዱ ይችላሉ የሚለው ነው አንዱ ሥጋታቸው፡፡ በመሆኑም እነዚህ ምክንያቶች በምርጫ ውጤቱ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ሊኖራቸው እንደሚችል ተናግረዋል፡፡ የምርጫ ውጤቱን ተከትሎ እንዳይከሰት ከወዲሁ ጥንቃቄ ሊደረግ እንደሚገባም መክረዋል፡፡

ዘጋቢ፡- ኃይሉ ማሞ

Previous article10ኛ ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪሚዬር ሊግ ጨዋታዎች ከነገ ጀምሮ ይደረጋሉ፡፡
Next articleአረንጓዴ ቢጫ ቀዩ ሰንደቅ ያልተውለበለበበት ብቸኛው ዓለም አቀፍ መድረክ