
ባሕር ዳር: መስከረም 11/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር አሁን ያለውን አንጻራዊ ሰላም ዘላቂ ለማድረግ የሚያስችል ውይይት እያካሄደ ነው።
የሰሜን ምዕራብ እዝ ምክትል አዛዥ ፣የባሕር ዳር እና አካባቢው ኮማንድ ፖስት ሰብሳቢ ብርጋዴል ጀኔራል ሙሉዓለም አድማሱ ጨምሮ የከተማ አሥተዳደሩ የሥራ ኀላፊዎች የሃይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ ወጣቶች እና ጥሪ የተደረገላቸው የከተማው ነዋሪዎች በውይይቱ ተሳትፈዋል።
የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ከንቲባ የሕዝብ ግንኙነት አማካሪ ጊዜው ታከለ የመወያያ ሰነዱን ባቀረቡበት ወቅት እንዳሉት የሰላም እጦቱ በክልሉ ኢኮኖሚያዊ እና ማኅበራዊ እንቅስቃሴ ላይ ተጽዕኖ እያደረሰ መኾኑን አንስተዋል። በችግሩም ቁሳዊ እና ሰብዓዊ ውድመት መድረሱን ነው ያስረዱት።
በክልሉ ብሎም በከተማው ለተፈጠረው የሰላም እጦት መነሻው የአማራ ክልል ሕዝቦች ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ችግር በተገቢው መንገድ አለመፈታት ፣ የማንነት ጥያቄ እና የሀገሪቱ ኢኮኖሚ ከሚያመነጨው ፍትሐዊ ተጠቃሚ አለመኾን እና የተሳሳቱ ትርክቶች አለመስተካከል ዋና ዋናዎቹ ናቸው ብለዋል።
ለችግሮቹ መፈታት የተጓዝንበት የትግል ሥልት ትክክል አለመኾን እና አዝጋሚ መኾን ለሰላሙ መደፍረስ በዋናነት የሚጠቀሱ ችግሮች ናቸው ብለዋል።
እነዚህ ችግሮች ተፈትተው ክልሉም ኾነ ከተማ አሥተዳደሩ ሰላሙ ተረጋግጦ በሰላም ወጥቶ የሚገባበት ሥራ መሠራት እንዳለበትም አንስተዋል።
ማኅበረሰቡ ችግር ፈጣሪዎችን ለይቶ በማውጣት ለሰላሙ ዘብ ሊቆም እንደሚገባም አማካሪው አሳስበዋል።
በውይይቱ ላይ አስተያየት የሰጡት የባሕርዳር ከተማ አሥተዳደር የሕዳሴ ቀበሌ ነዋሪው አቶ የሽዋስ ታፈረ የፌዴራሉ መንግሥት ፣የክልሉ መንግሥት እና ማኅበረሰቡ ችግሩን በጋራ ሊፈቱት እንደሚገባ አንስተዋል።
መምህር አብርሃም ሞላ መንግሥት እና አመራሩ በጋራ በመሥራት ችግሩን መፍታት እና ሰላሙን መመለስ አለባቸው ብለዋል።
ኢትዮጵያ የብሔሮች ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች መኖሪያ በመኾኗ ሕዝቦች በሰላም የሚኖሩባት እንጂ በግጭት የምትፈርስበት ምክንያት መኖር የለበትም ነው ያሉት።
ኢትዮጵያ ለበርካታ ሀገራት ምሳሌ ኾና የቆየች ብትኾንም አኹን በገጠማት ችግር ሰላሟ ደፍርሶ አንድነቷ ተናግቷል ይኽን በጋራ ሥራ መመለሥ ይገባልም ብለዋል።
በክልሉ ሰላም አለመኖር ሕጻናት ፣ሴቶች ፣አካል ጉዳተኞች እና አረጋውያን ጉዳት አስተናግደዋል። ይኽን ችግር በሰላማዊ መንገድ በመፍታት ሰላምን ማወጅ የማኅበረሰቡ እና የመንግሥት ድርሻ ነው ብለዋል።
የሰሜን ምዕራብ ዕዝ ምክትል አዛዥ ፣የባሕር ዳር ከተማ እና አካባቢዋ ኮማንድ ፖስት ሰብሳቢ ሜጀር ጀኔራል ሙሉዓለም አድማሱ በጦርነት እና በብጥብጥ የሚመጣ ሰላም እንደሌለም አስረድተዋል።
የውስጥ ችግሮችን ተመካክሮ እና ተወያይቶ መፍታት ያስፈልጋልም ነው ያሉት፡፡
የአማራ ክልል ሕዝብ ጥያቄዎችን በአግባቡ ለመመለስ የውስጥ አንድነት አስፈላጊ መኾኑንም ጠቁመዋል። ዛሬ መወያየት የቻልነው አንጻራዊ ሰላም በመኖሩ ነው ያሉት ሜጀር ጄኔራል ሙሉዓለም ሠርቶ ገቢ ማግኘት፣ ተምሮ ዳር መድረስና ነግዶ ማትረፍ የሚቻለው ሰላም ሲኖር ብቻ እንደኾነ አብራርተዋል።
የሀገር ሽማግሌዎች ፣ የሃይማኖት አባቶች ፣ ማኅበረሰቡ እና ወጣቶች ለሰላም ዘብ ሊቆሙ ይገባቸዋልም ነው ያሉት።
ዘጋቢ:- ትርንጎ ይፍሩ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!