“የሰላም እጦቱ የገቢ አሰባሰቡ ላይ ጫና ፈጥሯል” የአማራ ክልል ገቢዎች ቢሮ

49

ባሕር ዳር: መስከረም 11/2015 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል የተፈጠረው የሰላም እጦት ክልሉን በማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ ዘርፍ እየፈተነው ነው፡፡ በክልሉ የተፈጠረው የሰላም እጦት በገቢ አሰባሰቡ ላይ ጫና ፈጥሯል፡፡ በአማራ ክልል በወቅቱ መሰብሰብ የሚገባው ግብርም አልተሰበሰበም፡፡

የአማራ ክልል ገቢዎች ቢሮ የታክስ ጉዳዮች አማካሪ እንግዳወርቅ ገዛኸኝ ቢሮው በ2105 በጀት ዓመት 42 ነጥብ 85 ቢሊዮን ብር ለመሰብሰብ አቅዶ 38 ቢሊዮን ብር መሰብሰቡን አስታውሰዋል፡፡ በ2015 በጀት ዓመት የተሰበሰበው ገቢ ከ2014 በጀት ዓመት ጋር ሲነጻጸር 11 ነጥብ 1 ቢሊዮን ብር ብልጫ እንደነበረውም ተናግረዋል፡፡

በ2016 በጀት ዓመት 71 ነጥብ 65 ቢሊዮን ብር ለመሰብሰብ መታቀዱንም ገልጸዋል፡፡ በ2016 በጀት ዓመት የታቀደው እቅድ ከ2015 በጀት ዓመት ጋር ሲነጻጸር 67 በመቶ ብልጫ እንዳለው ተናግረዋል፡፡ በአዲሱ በጀት ዓመት የታቀደው እቅድ በ2015 በጀት ዓመት ከተሰበሰበው 88 ነጥብ 3 በመቶ እድገት እንዳለውም ገልጸዋል፡፡

በክልሉ የተፈጠረው የሰላም እጦት በገቢ አሰባሰቡ ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ መፍጠሩን ያነሱት አማካሪው ቢሮው እስካሁን ድረስ የእቅዱን 5 በመቶ ብቻ እንደሰበሰበም አስታውቀዋል፡፡ ግብር ያለ ሰላም ሊሳካ የማይችል መኾኑንም አንስተዋል፡፡

በክልሉ በተፈጠረው የሰላም እጦት የንግዱ ማኅበረሰብ ከቦታ ቦታ ተንቀሳቅሶ መሥራት አለመቻሉን፣ የምርት አቅርቦት ችግር መኖሩን እና የግብይት ሥርዓቱ ጤናማ አለመኾኑንም አመላክተዋል፡፡ የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴውም እየተገታ መኾኑን ነው የተናገሩት፡፡

በሰላም እጦቱ ምክንያት ባለሙያዎች በወቅቱ ግብር መወሰን፣ ማሰራጨት እና መሰብሰብ አለመቻላቸውንም አስታውቀዋል፡፡ የደረጀ ‘ሐ’ ግብር ከፋዮች ጥናት እየተጠና እንደነበር የተናገሩት አማካሪው በጸጥታ ችግር ምክንያት አንዳንድ ወረዳዎች ላይ ማጥናት አለመቻላቸውን እና አንዳንዶቹ ላይ ደግሞ ማጠናቀቅ አለመቻላቸውንም ገልጸዋል፡፡ ጥናታቸው የተጠናቀቁትንም ቢኾን ወደ ሥራ ማስገባት አልቻልንም ነው ያሉት፡፡

እስከ ሐምሌ 30 ድረስ የደረጃ ‘ሐ’ ግብር ከፋዮች ማጠናቀቅ እንደነበረባቸው ያስታወሱት አማካሪው 4 ነጥብ 2 በመቶ ብቻ መክፈላቸውንም ገልጸዋል፡፡

የደረጃ ‘ለ’ ግብር ከፋዮች እስከ ጳጉሜን መጨረሻ መክፈል ሲገባቸው በተፈለገው ልክ መሰብሰብ አለመቻሉንም ተናግረዋል፡፡ የአከራይ ተከራይ ግብርን ማስከፈል አለመቻላቸውንም ገልጸዋል፡፡ የሰላም እጦቱ በግብር ሥርዓቱ ከፍተኛ ጫና እንዳሳደረባቸውም አመላክተዋል፡፡

የሰላም እጦቱ በወቅቱ ግብርን በመሰብሰብ ለማኅበረሰብ ልማት ምላሽ እንዳይሰጥ እንደሚያደርግም ተናግረዋል፡፡ የግብር አሰባሰቡ መሻሻል ካላሳዬ ወረዳዎች እና ከተማ አሥተዳደሮች የጥሬ ገንዘብ እጥረት እንደሚገጥማቸውም ገልጸዋል፡፡

በ2016 በጀት ዓመት በርካታ ማሻሻያዎችን በማድረግ ገቢን ለማሳደግ ማቀዳቸውን የተናገሩት አማካሪው አሁን ባለው የሰላም እጦት በእቅዱ መሠረት መሄድ አልተቻለም ነው ያሉት፡፡ የሰላም እጦቱ ክልሉን እንደሚጎዳውም አመላክተዋል፡፡ አንጻራዊ ሰላም ባለባቸው አካባቢዎች ግብር ለመሰብሰብ ውይይቶችን እያደረጉ መኾናቸውንም ገልጸዋል፡፡

የታክስ ማጭበርበርና ስወራ በስፋት እንደሚስተዋል የተናገሩት አማካሪው የሰላም እጦቱ ለቁጥጥር ችግር መፍጠሩንም ጠቅሰዋል፡፡ ክልሉ ወደ ሰላም እንዲመለስ እና በኢኮኖሚ ከፍ እንዲል ሁሉም የበኩሉን እንዲወጣም ጥሪ አቅርበዋል፡፡ ግብር ከፋዮችን ግብርን በታማኝነት እና በቅንነት እንዲከፍሉም ጠይቀዋል፡፡

ዘጋቢ፡- ታርቆ ክንዴ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleበባሕርዳር ከተማ ኅብረተሰቡን ያሳተፈ የሰላም ውይይት እየተካሄደ ነው።
Next article“የሀገር ሽማግሌዎች፣ የሃይማኖት አባቶችና ወጣቶች ለሰላም ዘብ ሊቆሙ ይገባቸዋል።” ሜጀር ጀኔራል ሙሉዓለም አድማሱ