“የኮሌራ ክትባትን 98 በመቶ መስጠት ተችሏል” የደቡብ ጎንደር ዞን ጤና መምሪያ

47

ባሕርዳር፡ መስከረም 11/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በደቡብ ጎንደር ዞን የኮሌራ በሽታ የተከሰተ ሲኾን ለመቆጣጠር ሰፊ እንቅስቃሴ እየተደረገ ስለመኾኑ የዞኑ ጤና መምሪያ ገልጿል፡፡ የደቡብ ጎንደር ዞን ጤና መምሪያ ኀላፊ ሙላት አሻግሬ እንዳሉት በዞኑ 5 ወረዳዎች የኮሌራ በሽታ መከሰቱን ገልጸው በተለይም በደራ ወረዳ ሰፊ ሽፋን የነበረው እንደኾነ አስረድተዋል፡፡ በተለይም በዞኑ በሚገኙ ደራ ፣እብናት ፣ፎገራ ፣ወረታ እና በሊቦ ከምከም ወረዳዎች በሽታው መከሰቱን ነው ያስገነዘቡት፡፡

በሽታው እስካሁን 167 ሰዎች ላይ መታየቱን የተናገሩት አቶ ሙላት 124ቱ በደራ ወረዳ የተመዘገበ ስለመኾኑ ገልጸዋል፡፡

ኀላፊው ኮሌራ የግል እና የአካባቢ ንጽሕናን ባለመጠበቅ እና ምግብን በደንብ አብስሎ ካለመመገብ የሚመጣ እንደኾነ ገልጸው በተለይም ሰዎች በብዛት በሚገኙበት እና የንጽህና ኹኔታው በተጓደለ አካባቢ እንደሚከሰት ሁሉም ሊገነዘብ እንደሚገባ አመላክተዋል፡፡

በዞኑ የተከሰተውን የኮሌራ በሽታ ለመቆጣጠር ሁለት ቡድን ተዋቅሮ የቅድመ መከላከል እና የክትባት ሥራው እየተከናወነ ነው ብለዋል፡፡

ክትባት ያገኛሉ ተብለው ከታቀዱት 262 ሺህ ሰዎች ውስጥ ባለፉት 6 ቀናት ብቻ 98 በመቶው ክትባቱን እንዲያገኙ መደረጉንም ተናግረዋል፡፡

በዞኑ የቅድሚያ ቅድሚያ ክትባቱን ማግኘት ያለባቸው ሰዎች ተለይተው እየተከተቡ እንደኾነም ተናግረዋል። በሽታውን መከላከል እንዲቻል የግንዛቤ ፈጠራ ሥራዎች እየተሠሩ እንደኾነ ነው ኀላፊው የነገሩን፡፡ አቶ ሙላት ወቅታዊ የኾነው የሰላም እጦት ችግር የክትባት ግብዓቱን ከቦታ ቦታ ለማጓጓዝ እና የተሻለ ተደራሽ ለማድረግ የሚሠራውን ሥራ ፈታኝ እንዳደረገው ገልጸዋል። በችግር ውስጥ እየታለፈም ቢኾን ክትባቱን እና የመከላከል ሥራውን ለማከናወን ውጤታማ ሥራ መከናወኑን ተናግረዋል፡፡

ዘጋቢ፡- ምሥጋናው ብርሃኔ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleሉሲዎቹ የአፍሪካ ዋንጫ የመጀመሪያ ማጣሪያ ጨዋታቸውን ዛሬ ያደርጋሉ።
Next articleየአንስቴዥያ ህክምናን በማሻሻል በጥራት ለታካሚዎች ለማድረስ እየሠራ እንደሚገኝ የኢትዮጵያ አንስቴቲስቶች ማኅበር ገለጸ፡፡