እስራኤል የቤተ እስራኤላውያኑን መካነ መቃብር የቱሪስት መዳረሻ ልታደርግ ነው፡፡

901

ባሕር ዳር፡- ጥር 15/2012ዓ.ም (አብመድ) እስራኤል መካነ መቃብሩን የቱሪስት መዳረሻ ለማድረግ የግንባታ የመሠረት ድንጋይ አስቀምጣለች፡፡

የመቃብር ሥፍራው የሚገኘው በአማራ ክልል ሰሜን ጎንደር ዞን ዳባት ወረዳ በንከር “ጋንሽላሜ” በተባለ ቦታ ነው፡፡

በኢትዮጵያ የእስራኤል አምባሳደር ራፋኤል ማራቭና የሰሜን ጎንደር ዞን ዋና አስተዳዳሪ ወርቁ ለምለሙ ናቸው ትናንት ጥር 14/2012 የግንባታ መሠረተ ድንጋይ ያስቀመጡት፡፡

ቤተ እስራኤላውያን በጎንደርና አካባቢው ለብዙ ዓመታት መኖራቸውን የዳባት ወረዳ ባህልና ቱሪዝም ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ሰጠኝ አሌ ተናግረዋል፡፡ በአካባቢው ይኖሩ የነበሩ ቤተ እስራኤላውያን ጋን በመስራት ጥበብ ይታወቁ ስለነበር የአካባቢው ስያሜ “ጋንሽላሜ” እየተባለ ይጠራል፡፡

በኢትዮጵያ የእስራኤል አምባሳደር ራፋዬል ማራቭ ኢትዮጵያውያን የቤተ እስራኤላውያንን መካነ መቃብር በክብር ጠብቀው በማቆየታቸው አመስግነዋል፡፡ በዚህ አካባቢ ይኖሩ ከነበሩ ቤተ እስራኤላውያን ጋር በመተባበር አካባቢው የቱሪስት መዳረሻ እንዲሆንና መሠረተ ልማቶች እንዲሟሉለት እንደሚሠሩም ተናግረዋል፡፡

እስራኤል በኢትዮጵያ በጤና፣ በግብርናና በሌሎችም ዘርፎች እገዛ እያደረገች መሆኗ ይታወቃል፡፡

ዘጋቢ፡- ደስታ ካሳ

Previous articleወጣቱ የራሱን ታሪክ እንዲሠራ አባቶች አሳሰቡ፡፡
Next article10ኛ ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪሚዬር ሊግ ጨዋታዎች ከነገ ጀምሮ ይደረጋሉ፡፡