
ባሕር ዳር: መስከረም 11/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የጥላቻ ንግግር በሀገራችን ዘርፈ ብዙ መስቅልቅል ላስከተሉ ግጭቶች እንደ አንድ ገፊ ምክንያት ተደርጎ በብዙዎች ይጠቀሳል። ያደረሰውን ጉዳት የሚተነትኑ የጥናት ውጤቶችም ታትመዋል።
በጥላቻ ንግግር ሳቢያ የቤተሰብ አባሎቻችን ተገድለዋል ያሉ ዜጎችም ጉዳዩን ወደ ፍርድቤቶች ሲወስዱ ተስተውሏል።
ይህም ሆኖ ግን የጥላቻ ንግግር ድርጊት ሲቀንስ ወይም ሲገታ አልተስተዋለም። ይልቁንም ጊዜ እየጠበቀ ማገርሸቱን ቀጥሏል። ይህን ለማስተዋልም የማኅበራዊ ሚዲያ ገጾችን መከታተል በቂ ነው።
ባለፉት ጥቂት ሳምንታትም ሃይማኖት እና የብሔር ማንነት ላይ ትኩረት ያደረጉ የጥላቻ መልዕክቶች ተባብሰው ብቅ ብለዋል። እነዚህ እኩይ መልዕክቶች በተለይም በፌስቡክ፣ በቲክቶክና በተለያዩ ማኅበራዊ ትስስር ገፆች በስፋት በመጋራ ላይ ናቸው። ተዋናዮችም በሺዎች የሚቆጠሩ ተከታዮች ያላቸው ሰዎች መሆናቸው ስጋት ፈጥሯል።
መሰል አሉታዊ መልዕክቶች ግጭቶች እንዲባባሱና እንዲራዘሙ ከማድረግ ባለፈ አዳዲስ ግጭቶች እንዲፈጠሩ ምክንያት እየሆኑ ነው።
ስለሆነም ሁሉም ኀላፊነት የሚሰማው ዜጋ የጥላቻ መልዕክቶች ባለፉት ዓመታት ለተፈጠሩ ምስቅልቅሎች ያደረጉትን አሉታዊ አስተዋጾ በመረዳት የበኩሉን አወንታዊ ሚና ሊወጣ ይገባል።
የመጀመሪያው ማድረግ የምችለው አወንታዊ አስተዋጾ የጥላቻ መልዕክት ያላቸውን ይዘቶች በማዘጋጀትና በማሰራጨት ላይ አለመሳተፍ ነው። እንዲሁም የጥላቻ መልዕክት ያላቸውን ይዘቶች የሚያሰራጩ አካላትን አለማበረታትም ትልቅ ለውጥ ሊያመጣ የሚችል ድርጊት ይሆናል።
ሌላኛው በጉ አስተዋጾ ልናደርግበት የምንችለው መንገድ የጥላቻ መልዕክት ያላቸው ይዘቶችን የሚያሰራጩ አካላትን ማጋለጥና ያጋሩትን ይዘት ሪፖርት ማድረግ ነው።
የጥላቻ ንግግር ዒላማ ከሆኑ የማኅበረሰብ ክፍሎች ጋር መቆምም ኀላፊነት ከሚሰማው ዜጋ የሚጠበቅ ግዴታ መሆኑን ማስታወስ ያስፈልጋል።
ይህን ካደረግን የጥላቻ መልዕክቶችን ስርጭት በእጅጉ በመቀነስ ለራሳችን፣ ለበቤተሰቦቻችን፣ ለማኅበረሰባችን እና ለሀገራችን የተሻለ ከባቢ መፍጠር እንችላለን። መረጃው የኢትዮጵያ ቸክ ነው
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!