በቀሪ ቀናት በሚካሄደው የተማሪዎች ምዝገባ ማኅበረሰቡ የድርሻውን እንዲወጣ የምዕራብ ጎንደር ዞን ትምህርት መምሪያ ጥሪ አቀረበ።

45

ባሕርዳር፡ መስከረም 11/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በሀገሪቱ ተከስቶ የነበረው የኮሮና ወረርሽኝ እና በየጊዜው የሚከሰቱ ግጭቶች በመማር ማስተማሩ ላይ ትልቅ ሳንካ ፈጥረው ቆይተዋል ።

ትምህርት ሚኒስቴር የ2016 የትምህርት ዘመን መስከረም 14/ 2016 ዓ.ም የአንደኛው ወሰነ ትምህርት መደበኛ የክፍል ውስጥ ትምህርት እንደሚጀምር ይፋ ቢያደርግም በክልሉ በተከሰተው የጸጥታ እና ሌሎች ችግሮች ምክንያት በምዝገባ ሥርዓቱ ላይ አሁንም ችግር መፍጠሩን የምዕራብ ጎንደር ዞን ትምህርት መምሪያ ገልጿል።

የመምሪያው ምክትል ኀላፊ እርጥባን መስፍን እንዳሉት በዞኑ እስከ አሁን 50 በመቶ የሚኾነውን ተማሪ እንኳ መመዝገብ አልተቻለም። በዞኑ እስከ 8ኛ ክፍል ለመመዝገብ ከታቀደው 105 ሺህ 568 ተማሪዎች ውስጥ ማከናወን የተቻለው 44 በመቶ ገደማ ብቻ ነው። የሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎች ምዝገባ ከታቀደው ከ16 ሺህ 284 ተማሪዎች ውስጥ 18 በመቶ ብቻ መመዝገብ መቻሉን ገልጸዋል።

በዞኑ ከሚገኙት 239 ትምህርት ቤቶች ውስጥ 216 ብቻ ናቸው ወደ ሥራ የገቡት፡፡ በቋራ ወረዳ የሚገኙ 11 ትምህረት ቤቶች እና መተማ ወረዳ የሚገኙ 12 ትምህርት ቤቶች በአካባቢው በአጋጠመው ወቅታዊ የጸጥታ ችግር ምክንያት ምዝገባ አለመጀመሩን ገልጸዋል፡፡ በአጠቃላይ መተማ እና ቋራ ወረዳዎች በሚገኙ 33 ቀበሌዎች በተከሰተው የጸጥታ ችግር ምዝገባ ማካሔድ አለመቻሉን አንስተዋል፡፡

መስከረም 14/2016 ዓ.ም የመማር ማስተማር መርሃ ግብሩ እስኪጀምር ከሥራ ቀናት ውጭ ባሉት ቀናት ጨምር ምዝገባ ለማከናወን ለትምህርት ባለሙያዎች፣ መምህራን እና የወረዳ የሥራ ኀላፊዎች ስምሪት ተሰጥቶ አየተሠራ መኾኑን ምክትል ኀላፊዋ ገልጸዋል።

በቀጣይ ከመማር ማስተማር ሥራ ጎን ለጎንም የተማሪ ምዝገባው የሚቀጥል ይኾናል ነው ያሉት።

ምክትል ኀላፊዋ እንዳሉት ከተማሪ ምዝገባ ጎን ለጎን ከቋራ ውጭ ባሉ ወረዳዎች እና ከተማ አሥተዳደሮች የመጽሐፍ ሥርጭትም ተካሂዷል።

በዞኑ እስከ አሁን ከ5ኛ እስከ 8ኛ ክፍል ለሚገኙ ተማሪዎች ከ30 በላይ የትምህርት አይነቶች 30 ሺህ መጽሐፍት ተሠራጭቷል። ከ9 እስከ 12ኛ ክፍል ለሚገኙ ተማሪዎች ደግሞ በሶፍት ኮሚ የማባዛት ሥራ እየተሠራ ይገኛል ብለዋል።

እስከ አሁን ወደ ሥራ ቦታቸው ያልገቡ መምህራን እና ርእሳነ መምህራንም ወደ ሥራ ቦታቸው እንዲገቡ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

የትምህርት ጉዳይ የትውልድ ግንባታ ጉዳይ በመኾኑ ማኅበረሰቡ ልጆቹን በወቅቱ ወደ ትምህርት ቤት እንዲልክ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

ዘጋቢ፦ ዳግማዊ ተሠራ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleከመቅደላ ተዘርፈው የተወሰዱ የኢትዮጵያ ቅርሶች በለንደን ለሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ ተመለሱ፡፡
Next articleከ1 ነጥብ 6 ሚሊየን በላይ ለሆኑ ሰዎች ሕክምና የሚውል የወባ መድኃኒት ተሠራጨ።