ከመቅደላ ተዘርፈው የተወሰዱ የኢትዮጵያ ቅርሶች በለንደን ለሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ ተመለሱ፡፡

85

ባሕር ዳር: መስከረም 11/2015 ዓ.ም (አሚኮ) በ1868 በአጼ ቴዎድሮስ ዘመነ መንግሥት ተዘርፈው የተወሰዱ የኢትዮጵያ ቅርሶች በለንደን ለኢትዮጵያ ኤምባሲ ተመልሰዋል፡፡

ከተመለሱት ቅርሶች መካከል በ1868 ከመቅደላ የተዘረፈ የመድኃኒዓለም ታቦት፣ የልኡል አለማየሁ የጸጉር ዘለላ፣ ከብር የተሰሩና በነሃስ የተለበጡ ሶስት ዋንጫዎች እንዲሁም በዘመኑ ጦርነት ላይ የዋለ የጦር ጋሻ ይገኙበታል፡፡

የቅርሶቹ ርክክብ ሥነ ሥርዓት የተካሄደው ለንደን በሚገኘው ዝነኛው የአቴናየም ክለብ ሲሆን በመርኃ ግብሩ ሥነ ሥርዓት ላይ በዩናይትድ ኪንግደም የኢትዮጵያ መንግስት ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደርና ልዩ መልእክተኛን ጨምሮ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ልኡካን ቡድን፣ የብሔራዊ ቅርስ አስመላሽ ኮሚቴ ተወካይ፣ የሼሄራዜድ በጎ አድራጎት መስራች፣ የብሪታኒያ ፓርላማ አባላት፣ ቅርሶቹን ለማሰመለስ የተባበሩ እና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል፡፡

በመርኃ ግብሩ ላይ በዩናይትድ ኪንግደም የኢትዮጵያ መንግሥት ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደርና ልዩ መልእክተኛ አምባሳደር ተፈሪ መለሰ እንደተናገሩት “ዛሬ ባለቤቱ ለሆነው የኢትዮጵያ ሕዝብ የተመለሰው የመድኃኒዓለም ታቦት፣ የልኡል አለማየሁ ዘለላ ጸጉርና የተለያዩ ቅርሶች ለኢትዮጵያ ሕዝብ ሃይማኖት፣ ታሪክ ና ባህላዊ እድገት ከፍተኛ ጠቀሜታ ያላቸው ሀብቶች መሆናቸውን አስረድተዋል፡፡

አሳዛኝ በሆነው የመቅደላ ጦርነት ምክንያት የተዘረፉ የኢትዮጵያ ቅርሶች እሰከአሁን አለመመለሳቸው በመላው ኢትዮጵያዊ ልብና አእምሮ ውስጥ ጥያቄ ፈጥሮ መቆየቱን ተናግረዋል፡፡

እነዚህ ቅርሶች እንደ ቀላል ቁስ የሚታዩ ሳይሆኑ የአንድ ጥንታዊት ሀገር የታሪክ፣ የባህልና የማንነት መገለጫዎች ናቸው ብለዋል፡፡

ኤምባሲው ከመቅደላና ከሌሎች የኢትዮጵያ አካባቢዎች ተዘርፈው ወደ ዩናይትድ ኪንግደም የተጋዙ ቅርሶች እንዲመለሱ ለሚመለከታቸው የመንግስት አካላት፣ ለሁሉም የብሪታኒያ ሙዚየም የሥራ ኀላፊዎች፣ ለጥናትና ምርምር ተቋማት፣ ለቅርስ አስመላሽ እና ተሟጋቾች እንዲሁም ለበጎ አድራጎት ድርጅቶች በተደጋጋሚ ጥያቄ ማቅረባቸውን አስታውሰው አሁንም ይህ ጥረት ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል፡፡

ከነዚህ በጎ አድራጎት ድርጅቶች መካከል የሼሄራዜድ በጎ አድራጎት ድርጅት ከኤምባሲያችን ጋር በመተባበር ባደረገው ያልተቋረጠ ውትውታ ከሁለት ዓመት በፊት ከመቅደላ የተዘረፉ ከ 21 በላይ ቅርሶች እንዲመለሱ ተደርጓል፡፡ ከብሪታኒያ በአንድ ጊዜ ከተመለሱ የኢትዮጵያ ቅርሶች መካከል በወቅቱ ከፍተኛውን ቁጥር የያዘ እንደ ነበር አስታውሰዋል፡፡

በዛሬው እለት የተረከቧቸው ቅርሶቹም በተገቢው ቦታቸው እንዲቀመጡ ለማድረግ ወደ ኢትዮጵያ እንደሚሄዱ አረጋግጣለው ብለዋል፡፡

በዛሬው እለት በተደረገው የመድኃኒዓለም ታቦት፣ የልኡል አለማየሁ የጸጉር ዘለላ እና የሌሎች ቅርሶች አመላለስ ስነስርአት ላይ የተገኙት የብሔራዊ ቅርስ አስመላሽ ኮሚቴ አባል ፕሮፌሰር አሉላ ፓንክረስት ከብሪታኒያ የኢትዮጵያ ቅርሶች እየተመለሱ ያሉበት ሁኔታ ይበልጥ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ተናግረው በዛሬው የርክክብ ሥነሥርዓት ላይ ከ10ሺ ኪሎ ሜትር በላይ ተጉዘው የልኡል አለማየሁ የጸጉር ዘለላን ለመመለስ የመጡ የኒዊዝላንድ ዜጎች ጭምር ምስጋና ይገባቸዋል ብለዋል፡፡

የሼሄራዜድ በጎ አድራጎት መስራች ጣሂር ሻህ በበኩላቸው የታቦቱና የቅርሶቹ መመለስ ለኢትዮጵያ ሕዝብ ምን ማለት እንደሆነ እንደሚያወቁና፣ የሁለቱን ሀገራት ግንኙነት ይበልጥ የሚያጠናክር እንደ ሆነም ተናግረዋል፡፡

የብሪታኒያ ፓርላማ አባል ሎርድ ፖል ቦቲንግ በበኩላቸው ጥንታዊና ታሪካዊ የሆነቸው ኢትዮጵያ የማንነቷ መገለጫ የሆኑት ቅርሶቿ እንዲመለሱ ጥረት ሲደረግ መቆየቱን አስታውሰው፣ በዛሬው እለት የተደረገው ርክክብ ተገቢ ተግባር በመሆኑ አሁንም ከኢትዮጵያ የተዘረፉ ቅርሶችን የብሪታኒያ ሙዚየሞች ባለቤቱ ለሆነው የኢትዮጵያ ሕዝብ እንዲመልሱ ጥሪ አቀርባለው ብለዋል፡፡

በ1868 ከመቅደላ ተዘርፈው ከተወሰዱት መካከል የመድኃኒዓለም ታቦት አንዱ ሲሆን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የልኡካን ቡድን እንዲረከበው ተደርጓል፡፡

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ልኡክን የመሩት መጋቢ ሀዲስ ቀሲስ አባተ ጎበና እንደተናገሩት በ1868 ከመቅደላ የተዘረፈው የመድኃኒዓለም ታቦት እንዲመለስ መደረጉ ለኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ላቅ ያለ ሃይማኖታዊ ፋይዳ ያለው መሆኑን ገልጸው፣ ታቦቱ በተገቢው የሃይማኖት ስርአት ተይዞ ወደ ሀገሩ በቅርቡ እንደሚገባ ገልጸዋል፡፡

ምንጭ:በለንደን የኢትዮጵያ ኤምባሲ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየኢትዮጵያ ሴቶች ብሔራዊ ቡድን ለ2024 የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ከቡርንዲ አቻው ጋር ይጫዎታል፡፡
Next articleበቀሪ ቀናት በሚካሄደው የተማሪዎች ምዝገባ ማኅበረሰቡ የድርሻውን እንዲወጣ የምዕራብ ጎንደር ዞን ትምህርት መምሪያ ጥሪ አቀረበ።